🌱 “ያለ ዛፍ ጥላ፣ ያለ ዕውቀት መላ የለም” ኢትዮጵያውያን

5

 

ዛፍ ምድር የቆመችበት አንደኛው ባላ ነው። ለሰው ልጆች እና በጥቅሉ ለምድራችን ሕልውና ፍጹም አስፈላጊ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች እንደኾኑም ይታመናል።

ለሰው ልጆች ዋነኛ የኦክስጅን እና የምግብ ምንጭ በመኾን ሕይወትን ያስቀጥላሉ። የብዙዎቹ ባሕላዊ እና ዘመናዊ መድኃኒቶች መሠረት እንደኾኑም ይነገራል። ለሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች መሟላት ዋነኛ ምንጭም ናቸው። ምግብ፣ ልብስ እና መኖሪያ ቤት ያለ እነሱ አይታሰቡም። ያለ ዕጽዋት !

በዚህ ጽሑፍ ዕጽዋት በዚህ ልክ ለምድራችን አስፈላጊ ከኾነ በሰው ልጅ ዘንድ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶታል የሚለውን መቃኘት ነው። ከችግኝ ተከላ እና ከዛፎች እንክብካቤ ጋር በተያያዘ በተለይ በአካባቢ ጥበቃ የትውልድ ቅብብሎሽ ዙሪያ በርካታ ታዋቂ ቀደምት አባባሎችን እናገኛለን። እነዚህ አባባሎችም ሀገራት በጥቅሉ የሰው ልጅ በየዘመናቱ ለዕጽዋት የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክቱ ኾነው እናገኛቸዋለን።

ጥቂቶቹን እንመልከት፦

🌱 “ዛፍ ለአፈሩ፥ችግኝ ለሀገሩ”

ኢትዮጵያውያን ዕጽዋት እና ወጣቱ ትውልድ ሀገር የመጠበቅ እና የማጽናት ሚናውን ለማስረጽ “ዛፍ ለአፈሩ፣ ችግኝ ለሀገሩ” በማለት በቅኔ ይናገራሉ። አባባሉ ሁለት እርስ በርስ የተያያዙ ማኅበራዊ እና ተፈጥሯዊ ዕውነታዎችን ያነጻጽራል።

ትላልቅ ዛፎች ስሮቻቸውን ወደ መሬት በመስደድ አፈር በጎርፍ እና በንፋስ እንዳይጠረግ አቅፈው በመያዝ ለአፈር ዋስትና እንደኾኑ ኹሉ ለአንድ ማኅበረሰብም አንጋፋ እና በዕውቀት የበሰሉ ታላላቆች የሀገርን ባሕል፣ ታሪክ እና አንድነት ጠብቀው ለማቆየት ከፍ ያለ ሚና እንዳላቸው ለማስገንዘብ “ዛፍ ለአፈሩ” ይላሉ።

“ችግኝ ለሀገሩ” ሲሉ ደግሞ የቀጣይ እጣ ፋንታን አሻግረው መመልከታቸው ነው። ዛሬ የሚተከል ችግኝ ነገ አድጎ ትልቅ ዛፍ ይኾንና ለምድር ጥላ እና ፍሬ እንደሚሰጥ ኹሉ የዛሬ ወጣቶች እና ሕጻናትም በአግባቡ ካሳደግናቸው ነገ የሀገር አለኝታ፣ ጠባቂ እና መሪ ይኾናሉ።

🌱 “ያለ ዛፍ ጥላ፣ ያለ ዕውቀት መላ የለም” ሌላኛው የኢትዮጵያውያን ጥልቅ ፍልስፍናዊ አባባል ነው። ተፈጥሮአዊ ዕውነታን ከሰው ልጅ አዕምሯዊ ብስለት ጋር በማዛመድ የነገሮችን አስፈላጊነት በጉልህ አሳይተውበታል።

ያለ ዛፍ ጥላ አለመኖሩ ተፈጥሯዊውን ዕውነታ ነው። በአካባቢያችን ዛፎች ከሌሉ ከፀሐይ መጠለል አንችልም። የዛፍ ጥላ አካላዊ ሰላምን፣ ምቾትን የሚወክል ሲኾን ያለ ዕጽዋት ሕይወት ምድረ በዳ እንደምትኾን መግለጻቸው ነው።

“ያለ ዕውቀት መላ የለም” የሚለው ደግሞ የሰው ልጅን ለችግሮች መፍትሔ የመስጠት አቅምን ያሳዩበት ነው። በሕይወቱ የሚያጋጥሙትን የኑሮ፣ የኢኮኖሚ፣ የጤና እና የማኅበራዊ ሕይወት ፈተናዎች ተቋቁሞ ለማለፍ ዕውቀት ያስፈልገዋል ለማለት የተጠቀሙት አባባል ነው።

🌱 “አንድ ማኅበረሰብ ታላቅ የሚኾነው ሽማግሌዎች ጥላው ሾር እንደማይቀመጡበት እያወቁ ዛፎችን ሲተክሉ ነው”

ይህን የሚሉት ግሪካዊያን ናቸው። ዕውነተኛ ታላቅነት እና ሥልጣኔ የሚለካው ለራስ ብቻ ሳይኾን ለወደፊቱ ትውልድ በማሰብ ለሚደረግ ራስን የመሠዋት በጎ ተግባር ነው ማለታቸው ነው። የተከሉትን ችግኝ ተካዮቹ ራሳቸው እንደማይበሉት ወይም ከጥላው ሥር እንደማያርፉበት እያወቁ ዛፍ መትከላቸው ለነገው ትውልድ ያላቸውን ጥልቅ አሳቢነት ያሳያል እንደማለት ነው።

🌱 “ዛፍ ለመትከል ከኹሉ የተሻለው ጊዜ ከሃያ ዓመት በፊት ነበር። ሁለተኛው የተሻለው ጊዜ ደግሞ አሁን ነው”

ይህን ግሩም አባባል የሚጠቀሙት ደግሞ ቻይናውያን ናቸው። የሚጠበቅብንን ባለመሥራታችን ከመጸጸት ይልቅ አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ ለማስተማር ይጠቀሙበታል።

በተጨማሪም ቻይናውያን “በጥላው ሾር ዛሬ የተቀመጥነው፣ ከዓመታት በፊት አንድ ሰው ዛፍ ስለተከለልን ነው” ይላሉ። ዛሬ የምናገኘው ንጹሕ አየር፣ ሰላም እና ደስታ የጥንቶቹ አባቶቻችን የልፋት ውጤት መኾኑን፤ ያለፈውን ትውልድ ውለታና አሻራ እንድንገነዘብ እና እኛም ለቀጣዩ ትውልድ የምናርፍበት ጥላ ማዘጋጀት እንዳለብን ለማስገንዘብም የሚጠቀሙት አባባል ነው።

🌱 “ምድር ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትኾን ከልጆቻችን የተበደርናት ጭምር ናት”

ሕንዳውያን የተፈጥሮን እና የትውልድ ትሥሥርን በአባባላቸው ሲገልጹ “ምድር ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትኾን ከልጆቻችን የተበደርናት ጭምር ናት” ይላሉ። ተፈጥሮ እንደፈለግን የምናጠፋው የኛ የግል ንብረት ሳይኾን ለወደፊቱ ትውልድ በኀላፊነት ጠብቀን ማቆየት ያለብን የአደራ እቃ መኾኑን ያስገነዝባሉ። በየዘመናቱ የሚመጣው ትውልድ ቀደምቶቹ ባቆዩለት ሀብት ከመመጻደቅ ይልቅ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ምድርን ለማስተላለፍ መሥራት እንደሚጠበቅበት የሚነግር ጥብቅ መልዕክትንም አዝሏል።

🌱 “ዛፍ የሚተክል ሰው ሌሎችን የሚወድ ነው”

ይህን የሚሉት ደግሞ እንግሊዛውያን ናቸው።ዛፍ መትከል ከራስ በላይ ለትውልድ፣ ለሀገር እና ለዓለም ማሰብ መኾኑን ለማስገንዘብ ጥቅም ላይ የዋለ አባባላቸው ነው። ዛፍ መትከል ፍፁም ራስ ወዳድነት የሌለበት ተፈጥሮን፣ እንስሳትን እና የሰው ልጅን ለመጥቀም የሚከናወን ተግባር መኾኑን ገልጸውበታል።

በጥቅሉ ዕጽዋት ለምድራችን ጋሻ ናቸው። ጎጂ የኾነውን ካርቦንዳይኦክሳይድ ጋዝ በማስወገድ የአየር ንብረት መዛባትን እና የምድር ሙቀትን ይቆጣጠራሉ።

ዕጽዋት ሥራቸውን በምድር ውስጥ በመዘርጋት አፈርን አቅፈው በመያዝ በጎርፍ እና በንፋስ እንዳይሸረሸር የሚከላከሉበት የተፈጥሮ ጥበብ ግሩም ነው። በውኃ ዑደት ውስጥ ባላቸው ከፍተኛ ተሳትፎ ዝናብ በአግባቡ እንዲዘንብ ማድረጋቸው ደግሞ ግሩም የተፈጥሮ ምስጢር ነው።

በዚህ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለችግኝ ተከላ ትኩረት የተሰጠውም የሰው ልጅን ሕልውና የመጠበቅ ጉዳይ በመኾኑ ነው።

በዚህ ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ ነው። ሀገር በቀል ዕፅዋት፣ ለእንስሳት መኖ እና ለምግብ ዋስትና የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ። ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ይካሄዳል።

ችግኝ ስንተክል የራሳችንን ሕይወት እያስቀጠልን እና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ምድርን እያስረከብን መኾኑን በመረዳት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ በመትከል እንሳተፍ መልዕክታችን ነው።

#Ameco #Ethiopia #GreenLegacy #ClimateActionEthiopia

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_26_2018_ዓ_ም

✍️ በአድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌳 አረንጓዴ አሻራ – የኢትዮጵያ የተስፋ ትንፋሽ፣ የትውልድ አደራ እና የ56 ቢሊዮን ችግኞች ታሪካዊ ጉዞ
Next articleበጥሩ ብርሃን መሠረታዊ ፖሊስ ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የሠለጠኑ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ተመረቁ።