
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይኾን ሀገርን ከበረሃማነት የመታደግ፣ የኢኮኖሚ አቅምን የመገንባት እና ለቀጣይ ትውልድ ምቹ ሥነ-ምኅዳርን የማስረከብ ጥልቅ ሀገራዊ ራዕይ ነው። በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት ሲጀመር ዋነኛ መነሻ ምክንያቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ የመጣውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን መታደግ ነበር።
የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው የዝናብ እጥረት፣ ድርቅ፣ የአፈር መሸርሸር እና የግብርና ምርታማነት መቀነስ ሀገሪቱን አሳሳቢ አደጋ ውስጥ ጥሏት ስለነበር ይህንን አደጋ ለመቀልበስ እና ሚዛኑን የጠበቀ ተፈጥሮን ለመመለስ መርሐ ግብሩ ወሳኝ የመፍትሔ እርምጃ ኾኖ ተጀመረ።
ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያውያን በየክረምቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ዓለምን ያስደነቀ ታሪክ ሠርተዋል። የዚህ ያላሰለሰ የተከላ ጥረት አንፀባራቂ ውጤት 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በደን እንዲሸፈን ማስቻሉ ነው። የተራቆቱ ተራሮች አረንጓዴ ለብሰዋል፣ የደረቁ ምንጮችም ማፍለቅ ጀምረዋል።
መርሐ ግብሩ የጥቂቶች ብቻ ሳይኾን የብዙኀን መኾኑን የሚያረጋግጠው ከ25 ሚሊዮን ዜጎች በላይ (ከሕጻናት እስከ አዛውንት) በየዓመቱ በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን ማኖራቸው የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬት በዛፎች ብዛት ብቻ ሳይኾን ባመጣው ሥነ-ምኅዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ ይለካል። የደን ሽፋኑ ማደግ የአካባቢን አየር ንብረት ከማስተካከል ባለፈ የአፈር መሸርሸርን አስቁሟል፤ ለግድቦች አስጊ የኾነውን የደለል ክምችት ቀንሷል።
በአማራ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደን ምርምር ዳይሬክተር እና ከፍተኛ ተመራማሪ ምናለ ወንዴ (ዶ.ር) አሁን ላይ ያለው የችግኝ ተከላ ከሁለንተናዊ የተፋሰስ ልማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ብለዋል። በላይኛው ተፋሰስ የሚሠሩ ሥራዎች ታችኛውን የሚታደጉ መኾን እንደሚኖርባቸው፣ ይህም አፈርን ከጥፋት ከመታደግ እና እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ሀብቶች በደለል እንዳይሞሉ ለመከላከል ይረዳል ነው ያሉት።
በኢኮኖሚው ዘርፍ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ከፍተኛውን በመቶኛ የሚይዙት እንደ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ እና ቡና ያሉ ፍራፍሬ እና ችግኞች በመኾናቸው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ለውጭ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአረንጓዴ አሻራን አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማስረዳት የሚሞክሩት ተጨባጭ ገቢ በተገኘባቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ከፍ ባደረጉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ችግኞች ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛው አቦካዶ ላኪ ሀገር ኾናለች። ኢትዮጵያ ለ17 ዓመት ቡና ወደ ውጭ በመላክ ያገኘችው ገቢ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ነው። በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ፣ በዓለምም ከብራዚል እና ኮሎምቢያ በመቀጠል ሦሥተኛዋ ቡና ላኪ ሀገርም ኾናለች። እነዚህ ሁሉ የአረንጓዴ አሻራ ውጤቶች መኾናቸውን ጠቁመዋል።
በችግኝ ጣቢያዎች ዝግጅት እና እንክብካቤ የተፈጠረው የሥራ ዕድልም በቀላል የሚታይ አይኾንም። መርሐ ግብሩ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያውያን ለአንዲት ሀገር በጋራ እንዲቆሙ ያደረገ ትልቅ የማስተሳሰሪያ ድልድይም ኾኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረንጓዴ አሻራ ማለት ለትውልድ የምናወርሰው ህያው ሀውልት መኾኑን ለትርጉሙ ጥልቀት አጽንኦት በመስጠት ደጋግመው ገልጸዋል። ዛፍ መትከል ማለት ተስፋን መትከል ነው፤ ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ነገ ለልጆቻችን ጥላ፣ ምግብ እና ንፁህ አየር ይኾናል በማለት የጉዳዩን አንገብጋቢነት እና ሀገራዊ ፋይዳ ያሰመሩበት ንግግራቸው ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ታይቷል። አረንጓዴ አሻራ ድህነትን የምንፋለምበት፣ የተራቆተች ሀገራችንን አልብሰን ክብሯን የምንመልስበት ትልቅ ጦር ሜዳችን ነው በማለትም የሕዝቡን የሞራል ልዕልና ገንብተዋል።
ይህ ሁሉ ድል ተደምሮ የዘንድሮው የስምንተኛው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን የልማት ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ኾኗል። የዘንድሮው ተከላ ሲጠናቀቅ በስምንት ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ 56 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸው ይበሰራል። ይህም በዓለም ታሪክ ወደር የማይገኝለት አስደናቂ የሥነ-ምኅዳር መልሶ ግንባታ ስኬት ኾኖ በታሪክ የሚዘከር ይኾናል።
መጭው ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድጋሚ ዓለምን የሚያስደምምበት ታሪካዊ ዕለት ይኾናል። በዚህች አንዲት ጀንበር ብቻ 800 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ። ይህ ዕለት ሕዝቡ ዳግም ተባብሮ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ለተፈጥሮ ያለውን ክብር እና ለቀጣዩ ትውልድ ያለውን ኀላፊነት በተግባር የሚያሳይበት ደማቅ አሻራ ኾኖ በታሪክ መዝገብ ይሰፍራል።
#Ameco #GreenLegacy #Ethiopia
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_26_2018_ዓ_ም
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
