
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የክልሉን የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ግብ መሠረት በማድረግ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
በመድረኩ የመሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ እንደገለጹት ቢሮው የገጠር እና የከተማ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓትን በማዘመን እንዲሁም መረጃዎችን በዲጂታል መንገድ በማደራጀት ረገድ ውጤታማ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል።
ይህም ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊ እና ፈጣን የኾነ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ኀላፊው በክልሉ በሚገኙ 144 ወረዳዎች ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ አሥተዳደር ሥርዓትን (ካዳስተር) ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በዚህም የበርካታ አባወራዎችን እና እማወራዎችን የካዳስተር እና የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በእጃቸው እንዲገባ በማድረግ የዜጎችን የመሬት ባለቤትነት እና የመጠቀም መብት በሕግ ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።
ይህ የማዘመን ሥራ የአርሶ አደሮችን ሕይወት የቀየረ ተግባራዊ ውጤት ማምጣቱም ተገልጿል። የመሬት ውርስ፣ ስጦታ፣ ልውውጥ፣ ኪራይ እና የብድር አሠራሮች ግልጽ እና ቀልጣፋ በኾነ መንገድ እንዲከናወኑ አስችሏልም ነው የተባለው።
አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታቸውን በማስያዣነት (ኮላተራል) በመጠቀም ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ብድር እንዲያገኙ ማድረግ ስለመቻሉም ቢሮ ኀላፊው አረጋግጠዋል።
ተቋሙ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለከተማ ልማት የሚኾኑ መሬቶችን ለይቶ በማዘጋጀት እና በማስተላለፍ ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በከተሞች ለልማት ሥራዎች ሲባል ከይዞታቸው ለተነሱ ነዋሪዎች ተመጣጣኝ፣ ፍትሐዊ እና ወቅቱን የጠበቀ ካሳ እንዲከፈላቸው በማድረግ በኩል የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በከተማ እና በገጠር አካባቢዎች የሚታዩ ሕገ-ወጥ የመሬት አጠቃቀም እና የመሬት ወረራዎችን በሙሉ አቅም ከመግታት አንጻር ክፍተቶች እንደነበሩም ተመላክቷል።
ቢሮው በ2019 በጀት ዓመት በ25 ዓመቱ አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ላይ የተመሠረቱ ግቦችን ለማሳካት የመሬት አሥተዳደር አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ማዘመን፣ ሕገ-ወጥ አሠራሮችን እና የመሬት ወረራ ቁጥጥርን ማጠናከር እንዲሁም ለልማት ተነሽዎች የካሳ ክፍያ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
