
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
የቢሮው ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ክልሉ በማዕድን፣ በግብርና እና በሰው ኃይል ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ሰፊ አቅም ያለው መኾኑን ገልጸዋል።
ቢሮው ነባር ማነቆዎችን ለመፍታት እና አሠራርን ለማዘመን፣ አዳዲስ የአሠራር ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት መስጠቱንም አስታውቀዋል።
ቢሮ ኀላፊው እንዳሉት ባለፈው በጀት ዓመት:-
በቦርድ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ታች ወርደው በተግባር ሳይተረጎሙ በየመዝገቡ ላይ መቅረት፣ በተቋማት መካከል ዘላቂ እና የተቀናጀ አሠራር አለመኖር፣ በየደረጃው ላሉ ፕሮጀክቶች በቂ ባለሙያ መድቦ የቅርብ ድጋፍ አለማድረግን ጠቁመዋል።
የዘንድሮው ዕቅድ ከፍተኛ ግብን መነሻ አድርጎ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። የዕቅዱ ዋና ግብ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና በማዕድን ዘርፎች ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደኾነ ነው የተናገሩት። ይህን ለማሳካት ከፍተኛ ዲሲፕሊን እና የቅርብ ክትትል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአገልግሎት ብልሽት የክልሉን የኢንቨስትመንት ገጽታ ስለሚያበላሽ መልካም አስተናጋጅነትን መርሕ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
