“መንግሥት ለአማራ ክልል ሕዝብ የመልማት ፍላጎት በትኩረት እየሠራ ነው ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

13

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቆይታቸውም በአማራ ክልል ለዘመናት የቆዩ የልማት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ለ18 ዓመታት የተጓተተው የመገጭ ግድብ ወደ ሥራ ለመግባት መቃረቡን፤ ማዳበሪያ እና ቴክኖሎጂን በማስፋፋትም የክልሉ ዓመታዊ ምርት ከ90 ወደ 205 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉን፣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ሰፊ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪ እና መሠረተ ልማት ረገድ የባሕር ዳር፣ የደብረ ብርሃን እና አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ ትልልቅ የሲሚንቶ፣ የሴራሚክ እና የዘይት ፋብሪካዎች ተገንብተዋል ብለዋል።
የጸጥታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የክልሉ የመንገድ ሽፋን ከ2 ሺህ ወደ 4 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ማደጉን፣ 61 የመንገድ ፕሮጀክቶች በመሠራት ላይ መኾናቸውን፤ የአየር ማረፊያ ተርሚናሎች እና የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የጎርጎራ፣ የፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ዕድሳት፣ የላሊበላ ጥገና እና ሌሎችም የቱሪዝም ፕሮጀክቶች እንዲሁም በ32 ከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት የክልሉን ገጽታ ከመቀየር አልፎ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ነው ያሉት።

የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማትን ከማስፋፋት አኳያም የጠቅላላ ሆስፒታሎችን ቁጥር ወደ 20፣ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታሎች ደግሞ ከ43 ወደ 90 ማድረስም ተችሏል ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ሽፋን ከ25 በመቶ ወደ 40 በመቶ ከፍ ያለ ሲኾን ግዙፍ የኅይል ማስተላለፊያዎችም ተገንብተዋል ነው ያሉት።

በዲጂታል ዘርፍም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶች የኮደረስ ሥልጠና መውሰዳቸውን፣ የሞባይል ተጠቃሚዎች 16 ሚሊዮን መድረሱን እና የ4G እና 5G ኔትወርኮች መስፋፋታቸውንም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም ባለፉት ዓመታት የተሠሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለቀጣይ ብሩህ ተስፋ የሚሰጡ መኾናቸውን አስገንዝበዋል።

#Ethiopia #AmharaRegion #Ameco #AbiyAhmed #PeaceBuilding #CurrentAffairs

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የኢትዮጵያ ሕዝብ በድምፁ ታሪክ ሠርቷል፤ ለሌብነትና ለመከፋፈል ‘በቃ’ ብሏል!” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 🇪🇹🕊️
Next article“መፈናቀልን እናስቀራለን ያሉ ኀይሎች አሁን ሰው ከቤቱ ወጥቶ መግባት እንዳይችል አድርገዋል”ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)