
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አስመልክቶ እና በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራ ክልል አካባቢዎች መልሶ ከማልማት አኳያ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ለኢትዮጵያ ያስገኘው ነገር የጥይት ተኩስ ድምጽ ቆሞ ልማት ላይ ለማተኮር መኾኑን ገልጸዋል። ይህም በምንም መስፈርት የአማራ ሕዝብን ሊጎዳው አይችልም ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ከለውጡ በኋላ በመስኖ እና በንጹሕ መጠጥ ውኃ፤ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በመንገድ፣ በግድብ እና መሰል ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች መከናዎናቸውን ዘርዝረዋል። ካለፉት 30 ዓመታት በብዙ እጥፍ የላቁ ሥራዎች በአማራ ክልል ተሠርተዋል ነው ያሉት።
እነዚህ ሥራዎች ብዙዎቹ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ነው የተሠሩት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለኾነም ስምምነቱ ልማት አምጥቷል ብለዋል።
ከኢትዮጵያም ባሻገር አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንደሚፈቱ አሳይቷል ነው ያሉት። ጦርነቱ በራሳችን በአፍሪካዊያን ስምምነት ላይ መደረሱ ለእኛም ለሌሎች አፍሪካዊያንም ተስፋን የሚያጭር ጠቃሚ ነገር መኾኑን ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት የፕሪቶሪያው ስምምነት ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይኾን ለኹሉም አካባቢዎች ጥቅም ያስገኘ ነው ብለዋል።
በትርጉም ስንመለከተው የአማራን ጥቅም ያሳጣ፣ አማራ ባለቤት ያልኾነበት ውይይት ነው የሚል ሐሜቶች ይሰማሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምምነቱ እንዲካሄድ የወሰነው ፓርቲው በመኾኑ በፓርቲው ውስጥ በሚገባን ልክ የመሳተፍ እድሉ የሰፋበት ስለኾነ የአማራ ክልል የውሳኔ አሻራ አለበት ብለዋል።
#Ameco #PretoriaAgreement #PmAbiyAhmed #Ethiopia
በአድኖ ማርቆስ
