“ሁሌም የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

7

 

የአማራ ክልል ምክር ቤት በምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እና ለምክር ቤት አባላት የምሥጋና እና ዕውቅ የመስጠት መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ምክር ቤቱ በርካታ የሕዝብ ፍላጎቶች የተወከሉበት እንደኾነ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ በበርካታ ፈተናዎች ያለፈ መኾኑንም አንስተዋል። በሥራ ዘመኑም የሚጠበቅበትን ኀላፊነት በሚገባ የተወጣ ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ መደበኛ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራው ገንቢ እንደነበርም አንስተዋል። አስፈጻሚውን በመቆጣጠር፣ የአስፈጻሚ ተቋማት ዕቅድ እንዲሳካ ሰፊ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት። በርካታ ሪፎርሞች እንዲሳኩ ሰፊ ድጋፍ ያደረገ እና ለቀጣይም ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

ለክልሉ ሕዝብ ሲሉ በርካታ የምክር ቤት አባላት የሕይወት መሥዋትነት የከፈሉ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ታሪክ የማይረሳው መኾኑን አንስተዋል። ሕይወታቸውን ላጡት የምክር ቤት አባላት ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የተለያየ ግፊትን ተቋቁመው በምክር ቤት አባልነታቸው የቆዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ለዴሞክራሲ ልምምድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለቀጣይም ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

መሪ እና ተቋም ለሕዝብ ተገዥ መኾን አለባቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ሁሌም የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም ይገባል” ብለዋል። ችግሮችን ተቋቁማችሁ የሕዝብን ጥቅም እና ፍላጎት የሚያስከብር ሥራ ለሠራችሁ የምክር ቤት አባላት ምሥጋና ይገባችኋል ነው ያሉት።

በምክር ቤት አባልነት ለሚቀጥሉ አባላት ቀሪው ዘመን የተቃና እንዲኾን ለአማራ ክልል ሕዝብ እና ለኢትዮጵያ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ወደ ፊትም በምክር ቤቱ ለሚቀጥሉ እና በተለያየ ሥራ ለሚሰማሩ የምክር ቤት አባላት እና መሪዎች የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም ሥራ እንዲሠሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመርሐ ግብሩ በምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ መሪዎች እና የምክር ቤት አባላት ምሥጋና እና ዕውቅና ተሰጥቷል።

#አሚኮ #AmharaRegionalState #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“መስዋትነትን ከፍለው ያለፉ የምክር ቤት አባላት በጀግንነት ሀገር አስቀጥለዋል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ