
የአማራ ክልል ምክር ቤት በምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እና ለምክር ቤት አባላት የምሥጋና፣ ዕውቅና የመስጠት እና ሎጎ የማስተዋወቅ መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ምክርቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ መክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ምክር ቤቱ በሥራ ዘመኑ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች እና የክልሉ መንግሥት ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
በዚህም ለአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ ለአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት፣ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና ለሌሎችም ሚዲያዎች ምሥጋና አቅርበዋል።
ወቅታዊ ችግር ባጋጠመ ጊዜ በክልላችን ጉባኤዎችን በስኬት እንድናካሂድ ላደረጉት የጸጥታ አካላትም ከፍ ያለ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
በየጊዜው በሚያጋጥሙ ችግሮች ሳይበገሩ የሕዝብ ድምጽነታቸውን ላረጋገጡ የምክር ቤት አባላትም ትልቅ ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
“በሥራ ላይ እያሉ መስዋትነትን ከፍለው ያለፉ የምክር ቤት አባላት በጀግንነት ሀገርን አስቀጥለዋል” ነው ያሉት። ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉም ብለዋል።
የምክር ቤት አባላት ሲያደርጉት የቆዩትን የላቀ ተሳትፎ በቀጣይም አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ኅብረብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጉዞም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዲሱን የምክር ቤት ሎጎ የማስተዋወቅ መርሐ ግብርም ተካሂዷል።
#አሚኮ #AmharaRegionalState #Ethiopia🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
