
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2018 ዓ.ም የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በክልሉ በ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ተግባራዊ ለማድረግ ከ1 ነጥብ 76 ቢሊዮን በላይ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ እና ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በማዘጋጀት የተከላ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ከ261ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በወል፣ በግለሰብ እና በተቋማት ደረጃ የተከላ ቦታዎች የመለየት እንዲሁም የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን በመግለጫው አመላክተዋል።
በተለይም የፍራፍሬ ችግኞች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በበጋ በመስኖም ጭምር በመደገፍ በተለያዩ አካባቢዎች በክላስተር የሙዝ፣ የፓፓዬ፣ የአቮካዶ እና ቡና ችግኞችን በስፋት ከማዘጋጀት ባለፈ ተከላ ሲከናወን ቆይቷል ነው ያሉት።
በዚህም ዘንድሮ ” ተስፋን እንትከል “በሚል መሪ መልዕክት በሀገር አቀፍ ደረጃ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ከተጀመረ በኋላ በክልሉም ሰኔ 18/2018 ዓ.ም በአቮካዶ ክላስተር ተከላ መጀመሩን አንስተዋል በመግለጫው።
እስካሁንም ከ1ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን የገለጹት ቢሮ ኅላፊው በሁሉም አካባቢዎች ከ189ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተሸፍኗል ነው ያሉት።
በክልሉ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከ10 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከሉን እና ከ1ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን ነው የገለጹት። በዚህም የደን ሽፋኑ ከ14 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 18ነጥብ 9በመቶ ከፍ ብሏል። የጽድቀት ምጣኔውም በአማካኝ ከ81በመቶ በላይ መድረሱን ነው የተናገሩት። ይህም ማኅበረሰቡ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ባለቤት ኾኖ የመንከባከ፣ የመጠበቅ እና ዘላቂነታቸው እንዲረጋገጥ በማድረጉ የመጣ ለውጥ ነው ብለዋል።
በዚህም ምርታማነት እንዲጨም፣ የውኃ አቅሞች እንዲጎለብት፣ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። ለአፈር እና ውኃ ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተም ነው ብለዋል። በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በተለይም በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ እና በፍራፍሬ ልማት የሥራ አማራጭ እንዲኾን እና ገቢያቸው እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።
እንደሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በተለይ ዕጽዋቶችን የመትከል እና የመንከባከብ ምሳሌ በመኾን በቀጣይ ኮፕ 32 የዓለም አቀፍ ጉባኤን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ እንዳስቻላት ተናግረዋል።
ለስምንተኛ ጊዜ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባለፉት ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ላይ የማተኮር ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏልም ብለዋል።
በዚህም በፊታችን ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሀገር ደረጃ ከ800 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ነው የገለጹት። በአማራ ክልልም 327 ሚሊዮን ችግኞች በ65 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም በመግለጫው አብራርተዋል። ለዚህም 3ሺህ 554 የተከላ ቦታዋች ተለይተዋል ነው ያሉት። ለአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በርካታ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።
ከታች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ የሚያስተባብሩ ከ4ሺህ በላይ ባለሙያዎች ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት። በተለይም በቀበሌ ደረጃ ያሉት በቀጥታ መረጃው በዕለቱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በኤስኤምኤስ ኮድ 699 መረጃዎች የሚላኩበት ሁኔታዎች ይፈጠራል ነው ያሉት ።
የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሁሉም ማኅበረሰብ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ በቂ ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል በመግለጫው። ችግኞችን ወደ ተከላ ቦታ በማጓጓዝ ጊዜያዊ የችግኝ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ በማድረግ ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። ለማኅበረሰቡም በቂ ግንዛቤ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
እስካሁንም ችግኞችን በመትከል ባለቤትነቱን እና ተሳታፊነቱን በማረጋገጥ የራሳቸውን አሻራ በማኖር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የነበሩት ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና በአጠቃላይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለሚከናወነው የአንድ ጀንበር የተከላ መርሐግብር በነቂስ ወጥቶ በመትከል በስኬት እንዲጠናቀቅ በግንባር ቀደምትነት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል። በዚህም ለቀጣዩ ትውልድ አሻራ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እስካሁን ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ መሳተፋቸውም ተመላክቷል።
አሚኮ #Ethiopia #GreenLegacy #ClimateActionEthiopia🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
