
ጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ29ኛ ጊዜ በቀን እና በማታ መርሐግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ከ430 በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።
በዕለቱ 90 ኢንተርፕራይዞችም የደረጃ ሽግግር አድርገዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኮሌጁ ቦርድ ሠብሣቢ ደብሬ የኋላን ጨምሮ የከተማዋ እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሥራ ኀላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች እና ተመራቂዎች ተገኝተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኮሌጁ ቦርድ ሠብሣቢ ደብሬ የኋላ በመርሐግብሩ እንደገለጹት ኮሌጁ በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና የልህቀት ማዕከል በመኾን ፈጠራን በማጎልበት ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራ ይገኛል።
ኮሌጁ ለተግባር ተኮር ሥልጠና ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ጠቁመው ይህም የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ ተማሪዎች ከዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እንዲራመዱ የሚያደርግ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ተስፋሁን መኮነን በበኩላቸው፣ ተቋሙ በ2017/18 የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በክልሉ የመጀመሪያ የኾነውን ዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋም ስታንዳርድ አይኤስኦ 21001:2025 የምስክር ወረቀት ማግኘቱን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ከወረቀት ንክኪ በመውጣት የኦንላይን ምዘናን ጨምሮ ዘመናዊ የዲጂታል አሥተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ በኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪያል ኮንትሮል ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 97 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የኾነው ተማሪ ታምሩ ተስፋሁን እና 3 ነጥብ 87 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የኾነችው ተማሪ ሳባ ግዛቸው የቤተሰቦቻቸውን እና የመምህራኖቻቸው ድጋፍ ከፍ ያለ መኾኑን ጠቁመው ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ማኅበረሰቡን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
#አሚኮ #ትምህርት🇪🇹
#ጎንደር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አደራጀው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
