
የአንድ ሀገር ዕድገት እና የሕዝቦች የጋራ ዕጣ ፈንታ በዋናነት የሚወሰነው የማይደፈሩ እና ለድርድር የማይቀርቡ ብሔራዊ ጥቅሞችን በማስከበር ረገድ ባለ የሕዝብ ቁርጠኝነት መኾኑ ብዙዎችን ያስማማል።
ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በባሕር በር ባለቤትነት መብቷ ዙሪያ የተገመዱ ብሔራዊ እና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች አሏት። እነዚህ ሁለት ትላልቅ ምሰሶዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ነጻነት እና ቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ይወስናሉ። በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ የህልውና እና የሉዓላዊነት ማሠሪያ አምዶች ተደርገው ይታያሉ።
🏗️ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ
ለኢትዮጵያዊያን በልማት ፕሮጀክትነት ብቻ አይገለጽም። ይልቁንም ከ 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ደም ላብ የገነባው የአንድነት ግማድ ነው።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሪያ የብርሃን ድልድይ እና በኢንዱስትሪ የሚመራ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት የተጣለ የትውልድ አሻራ ነው።
የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኀይል ፍላጎት በማሟላት ኢትዮጵያን የቀጣናው የኀይል ማዕከል ያደረገ፤ የውኃ ሀብቷን በሉዓላዊነት የመጠቀም ሕጋዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷን ያረጋገጠ የትውልድ ካስማ ነው።
በመኾኑም የግድቡ መሳካት የኢትዮጵያን የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ እና የኢኮኖሚ ነጻነት ማረጋገጫ ቀዳሚው ብሔራዊ ጥቅም ኾኗል።
🚢⚓ የባሕር በር ለኢትዮጵያ
ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት መብትን ማረጋገጥ የኢትዮጵያን የወጭ እና ገቢ ንግድ ከጥገኝነት ማላቀቅ ብቻ አይደለም ጥቅሙ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጣና ያላትን የጂኦ ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የደኅንነት ጥበቃ ሚና መልሶ ለመገንባት፤ ባሕርን በፍትሐዊነት የመጠቀም መብትን ማስከበር የሚያስችል ወሳኝ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ጭምር ነው።
በእርግጥም እነዚህን መሰል ትላልቅ ብሔራዊ ጥቅሞች ማሳካት የኢትዮጵያን ልዕልና፣ ሕልውና፣ የቀጣናውን መሪነት ሚና እና የወደፊት እጣ ፋንታ ያረጋግጣል። የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የልማት፣ የደኅንነት እና መሰል ስትራቴጂዎች ኹሉ መነሻ እና መድረሻ ኾነው የሚያገለግሉ ናቸው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እና የባሕር በር ባለቤትነት።
ብሔራዊ ጥቅሞችን ማሳጣት ደግሞ ሀገሪቱን በቀጣናው አቅም አልባ የማድረግ አደገኛ የጠላቶች እኩይ ፍላጎት ሲኾን በእነዚህ ጥቅሞች ላይ የሚሰነዘሩ ታሪካዊ ጥቃቶች እና ሴራዎች ኹሉ በግብጽ እና በኤርትራው ገዢ ግንባር ቀደም ጎንጓኝነት የሚፈጸሙ ኾነው እናገኛቸዋለን።
ታዲያ እነዚህ ሁለት እኩይ አካላት የኢትዮጵያ ጠላት መኾንን የመረጡት በአጋጣሚ አይደለም። የራሳቸውን ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት እና ቀጣናዊ የበላይነት ለማስጠበቅ የግድ ደካማ ኢትዮጵያ መኖር አለባት፤ ለዚህም የዕድገት መሠረቶቿን መጠቀም የለባትም የሚል አቋም ስላላቸው እንጅ። ለዚህም ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት በመጥመድ የልማት እጇን በማሰር የስትራቴጂያዊ ጥቅማቸው ዋስትና አድርገውም ይወስዱታል።
እናም እነዚህ ሁለቱ የኢትዮጵያ ደመኞች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማሳጣት በሚያደርጉት ስልታዊ ጥረት የውስጥ ባንዳዎች እና የሴራ ተላላኪዎች እንደ ዋነኛ መሣሪያ ኾነው ያገለግሏቸዋል።
በዚህ ረገድ ሕገ ወጡ ሕወሃት “አቤት ወዴት” ብሎ በመላላክ ወደር አይገኝለትም። ለሥልጣን እና ለቡድናዊ ጥቅሙ ካለው የበረታ ፍላጎት የተነሳ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፎ ለመስጠት ለካይሮ እና ለአስመራው ገዢ ተላላኪ ኾኖ እየሠራ ይገኛል።
ታሪካዊ ጠላቶች የሕገ ወጡን ሕወሃት እና የመሰል ቡድኖችን ባንዳነት ሽፋን በማድረግ ኢትዮጵያን በቀጣናው ደካማ፣ የተከፋፈለች እና ደሃ ሀገር አድርጎ ለማስቀረት ቀን ከለሊት ይተጋሉ።
ሕገ ወጡ ሕወሃት ሀገራዊ እና ሕዝባዊ አጀንዳ ከያዘ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከግብጽ እና ከኤርትራው ገዢ ጋር ማበር ባላስፈለገው ነበር። ለኢትዮጵያውያን የባንዳነት እና የሀገር ከሃዲነት መገለጫው ለየትኛውም ጥቅም ቢኾን እንኳን ከግብጽ እና ከኤርትራው ገዢ ጋር መተባበር ነው። ሕገ ወጡ ሕወሃት ባንዳ እና ያጎረሰውን እጅ ነካሽ ነው የምንለውም ለዚህ ነው።
ስለኾነም የሕወሃትን ጸረ ኢትዮጵያ አቋም እና አሰላለፍ ማጋለጥ እና መታገል የኢትዮጵያን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እና የሕዝቦቿን ህልውና መታደግ ታላቅ ሀገራዊ የትውልድ የቤት ሥራ ነው።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብን መጠበቅ እና የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማስመለስ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና የሕዝቦቿ የህልውና ምሰሶዎች ኾነው ለትውልድ የሚተላለፉ ምንዳዎች ናቸው። ስለኾነም እነዚህን ጥቅሞች ከውጭ ጠላቶች እና ከውስጥ ተላላኪዎች ሴራ መጠበቅ የኹሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ቀዳሚ ተግባር መኾን ይኖርበታል።
ያም አለ ይህ ይቺ የጀግኖች ምድር ኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ደመኞቿን ሴራ አክሽፋ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቿን አስከብራ እና ልዕልናዋን ጠብቃ በቀጣናው ያላትን መሪነት ያለጥርጥር ታስቀጥላለች።
#Ameco #Ethiopa #NationalInterest #UnitedEthiopia 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
