
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ተጠሪ ተቋማቱ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ በመገኘት የተለያዩ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አከናውነዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ በየደረጃው የሚከናወኑ ሰው ተኮር ሥራዎች የመደመር መንግሥት ዋና መገለጫ ባህሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታትም ለበርካታ ዜጎች መኖሪያ ቤት ገንብቶ በማስረከብ፣ አቅመ-ደካሞችን በማገዝ እና በማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን መደገፍ መቻሉን አብራርተዋል።
በጎዴ ከተማ በተካሄደው በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ500 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ ለ5 አባወራዎች አዲስ የቤት ግንባታ ተጀምሯል፤ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃን መሠረት ያደረገ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በስኬት ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሁሴን ሀሺ (ዶ.ር) በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በርካታ ዜጎችን ማገዝ መቻሉን ጠቅሰው፤ እነዚህ ተግባራት እርስ በእርስ በመደጋገፍ ለሚታወቀው የሶማሌ ማኅበረሰብ ተጨማሪ በጎ እሴት እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
በዕለቱ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች፣ ወላጆቻቸው እና የቤት ግንባታ የተጀመረላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው መግለጻቸውን የዘገበው ኢብኮ ነው።
#በጎ_ፈቃድ #የፌዴሬሽን_ምክር_ቤት #ኢትዮጵያ #ሰው_ተኮር_ሥራዎች
