በጸጥታ ችግር የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ ለማስተካከል መምህራን የድርሻቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።

3

 

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የመማር ማስተማር ሂደቱ የተቀላጠፈ እንዲኾን ለመምህራን እና ለሥራ ኀላፊዎች ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

በዚህም ለመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ለትምህርት ቤት የሥራ ኀላፊዎች ለሁለተኛ ዙር የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በደብረ ማርቆስ ከተማ መስጠት ተጀምሯል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ለሠልጣኞቹ በበይነ መረብ ባስተላለፋት መልዕክት የሀገርን ልማት እና ዕድገት ለማስቀጠል የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ሚና ያለው በመኾኑ መምህራንን ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ በየጊዜው ብቁ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሚሰጠው ሥልጠና በንቃት በመሳተፍ ለመማር ማስተማር ሂደቱ የተሻለ አቅምን መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ መምህራን ትምህርት ኮሌጂ ዲን ዜና ገብረ ማርያም ሠልጣኞች ሥልጠናቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እና ውጤታማ እንዲኾኑ ከባለፈው ዓመት በተሻለ ዝግጂት መደረጉን ተናግረዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ ባለፋት ዓመታት በዞኑ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በትምህርት ዘርፍ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ መምህራን የድርሻቸውን ሚና ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

ሥልጠናው የትምህርት ሥርዓቱን በውጤታማነት ለመምራት እና የሥራ ተነሻሽነትን አቅም የሚያሳድግ መኾኑን ገልጸዋል።

ሠልጣኞችም እንደዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች መዘጋጀታቸው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና አቅም ለማጎልበት እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።

በደብረ ማርቆስ መምህራን ትምህርት ኮሌጂ በሚሰጠው ሥልጠና 1ሺህ 167 የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና የትምህርት ቤት የሥራ ኀላፊዎች ተሳታፊ ናቸው።

#AMECO #ትምህርት #አማራክልል_ኢትዮጵያ🇪🇹

#ደብረ_ማርቆስ #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአፍሪካውያን በልብ ሕክምና ዘርፍ ኢንቨስት ሊያደርጉ ይገባል።
Next articleለዜጎች የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ማስረከብ።