አፍሪካውያን በልብ ሕክምና ዘርፍ ኢንቨስት ሊያደርጉ ይገባል።

1

 

በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የልብ እና የደም ቧንቧ ሕመም ቀውስ ለመታደግ ዓላማ ያደረገ የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር እና የፓን-አፍሪካ የልብ ሕክምና ማኅበር በጋራ ያዘጋጁት 11ኛው ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

“በአፍሪካ የልብ ሕክምና አገልግሎት ከእጥረት ወደ ዘላቂነት” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ የካርድዮሎጂ ምርመራ መሳሪያዎች እጥረት፣ የረጅም ጊዜ የተጠባባቂ ታካሚዎች ዝርዝር እና የሕክምና ተደራሽነት የዘርፉ ክፍተት ምክንያት ኾነው ተነስተዋል።

በጉባኤው በመላው አፍሪካ ፍትሐዊ የልብ ሕክምና አገልግሎትን የሚገድቡ ስር የሰደዱ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ አመላካች ሀሳቦች ተነስተዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ናትናኤል ታዬ ዲጂታል የጤና ቴክኖሎጂዎችን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) የታገዙ የልብ ምት መከታተያዎችን ማሰማራት፣ በገጠር አካባቢዎች የቴሌ-ካርዲዮሎጂ አገልግሎትን ማስፋፋት እና ታካሚዎች ለሕክምና ወደ ወጭ ሀገር የሚያደርጉትን ፍሰት ለመቀነስ ክልላዊ የሕክምና ማዕከላትን መገንባት የሚያስችል አቅምን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ፕሮፌሰር ሀቢብ ጋምራ፣ የፓን-አፍሪካ የልብ ሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ሲኾኑ የተቀናጀ አሕጉራዊ እንቅስቃሴ እና በአዲሱ የሕክምና ዘርፍ ላይ ያተኮረ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

ታዋቂ የልብ ሕክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር ኤልያስ ኦጎላ በበኩላቸው አፍሪካ በዓለም ደረጃ የችግሩን መጠን አንድ አራተኛ ትይዛለች ብለዋል። በጤና ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት በቀጥታ ለሰፊው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረት መኾኑንም አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

ዘላቂ የጤና ሥርዓትን ለመገንባት አባል ሀገራት በአቡጃ የገቡትን ቃል በመጠበቅ ከሀገራዊ በጀታቸው ቢያንስ 15 በመቶ ለሕዝብ ጤና መሠረተ ልማት መመደብ እንዳለባቸውም በጉባኤው ተመላክቷል።

የአፍሪካ የጤና ሥርዓቶች ተንቀሳቃሽ የኢኮካርዲዮግራፊ መሳሪያዎችን፣ በኤአይ የታገዙ የኦፕቲካል ምርመራዎችን እና በአፍሪካውያን የሚመሩ ክሊኒካዊ ጥናቶችን በማድረግ የአካባቢውን የጤና ሁኔታ መመለስ እንደሚገባም ተነስቷል።

የልብ ሕመምን እንደ አሕጉር ትኩረት ለመስጠት ውድ የኾኑ የሕክምና ቁሳቁሶችን በጋራ የመግዛት ሥርዓትን በመዘርጋት እና አሕጉር አቀፍ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ለመድኃኒት እና ለሕክምና ሥራዎች የሚወጣውን ወጭ መቀነስ ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።

#AMECO #የልብሕክምና #HealthAfrica #Cardiology🇪🇹

#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ሃናማርያም መስፍን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየአማራ ክልል የ2019 ዓመታዊ በጀት ከ402 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ኾኖ ጸደቀ።
Next articleበጸጥታ ችግር የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ ለማስተካከል መምህራን የድርሻቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።