በሀረሪ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ሕይወት በላቀ ደረጃ እየቀየረ ነው።

7

 

በሐረሪ ክልል በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እና የአብሮነት እሴትን በማጎልበት የዜጎችን ሕይወት በላቀ ደረጃ እየቀየረ እንደሚገኝ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌቱ ዋዬሳ ገልጸዋል።

በክልሉ በሚከናወኑ የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ዙሪያ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንደተመላከተው አገልግሎቱ አቅምን በመደመር እና ሀብትን በማቀናጀት አቅመ ደካሞችን እና አረጋውያንን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን እውን ለማድረግ አስችሏል።

በዚሁ መሠረት በዘንድሮው መርሐ-ግብር የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ 14 ዋና ዋና የበጎ ተግባራት ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ከተከናወኑት እና ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ዕድሳት እና መልሶ ግንባታ፣ የአካባቢ ንጽሕና ጥበቃ፣ የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ የማዕድ ማጋራት፣ የአዳዲስ እና ነባር የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እና ዕድሳት፣ የተማሪዎች ወንበር ጥገና እንዲሁም የማጣቀሻ መጻሕፍት ማሠባሠብ ሥራዎች ይገኙበታል።

አቶ ጌቱ አያይዘውም የመተጋገዝ እና የአብሮነት ባሕል ድህነትን ለማሸነፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር በመኾኑ መሪዎች የታቀዱትን ግቦች ሙሉ በሙሉ ለማሳካት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተጨማሪም በክልሉ በጳጉሜን ቀናት በሚከናወኑ መርሐ-ግብሮች ሁሉም የመንግሥት ተቋማት፣ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና መላው ሕዝብ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሚኮ #የበጎፈቃድ_ሥራ #በሀረሪክልል_ኢትዮጵያ

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_29_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየፈተና እና ምዘናዎች አገልግሎት በሊቦከምከም ወረዳ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት የትምህርት ቤት ግንባታ አስጀመረ።
Next article“የኅብረተሰብን ጤና መጠበቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና መሠረት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ