
የፌዴራል ፈተና እና ምዘናዎች አገልግሎት በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው።
በሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የፌዴራል ፈተና እና ምዘናዎች አገልግሎት ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ.ር) እና ምክትል ዳይሬክተሩ ተፈራ ፈይሳን ጨምሮ የአገልግሎቱ ከፍተኛ ሥራ አሥፈጻሚዎች፣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊዎች እና የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የፌዴራል ተቋማት ወደ ክልሎች ወርደው በዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ባወረዱት አቅጣጫ መሠረት የሚገነባ መኾኑ ተገልጿል።
የሚገነባው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲኾን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት እንደሚገነባ ተገልጿል።
የፌዴራል ፈተና እና ምዘናዎች አገልግሎት በወረዳው ለአላቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ500 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ደብተር፣ 12 እስክርቢቶ እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
በተጨማሪም የሥራ ኀላፊዎቹ በወረዳው ችግኝ ተክለዋል። ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን 10 ሺህ ችግኞችም ለወረዳው አበርክተዋል።
አገልግሎቱ ለችግኞች እና ለትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉ ከ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረጉን የፌዴራል ፈተና እና ምዘናዎች አገልግሎት ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
#አሚኮ#ትምህርት #አማራክልል_ኢትዮጵያ
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_29_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
