
የአማራ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ በሚገኘው 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ በ2019 በጀት ዓመት ለክልሉ የልማት ሥራዎች ማስፈጸሚያ በጀት 402 ቢሊዮን 285 ሚሊዮን 713 ሺህ 544 ብር ኾኖ አጽድቋል።
የ2019 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀቱ በ2018 በጀት ዓመት ከተመደበው የ78 ነጥብ 4 በመቶ ወይም የ176 ቢሊዮን 831ሚሊዮን 934 ሺህ 307 ብር ዕድገት እንዳለው የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡
ከዓመታዊ በጀቱ 71 ነጥብ 3 በመቶ የሚኾነው በክልሉ ከሚሠበሠብ ገቢ፣ 27 ነጥብ 6 በመቶ የሚኾነው ከፌዴራል መንግሥት ጥቅል የቀመር መደበኛ ድጋፍ ድርሻ እንዲኹም ቀሪው ደግሞ ከልዩ ልዩ ምንጮች እንደሚሸፈን ተገልጿል።
የተመደበው በጀት በዓመቱ ለዘላቂ ልማት ዕቅድ ማስፈጸሚያ፣ ለልዩ ልዩ ሪፎርሞች እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች፣ ለድህነት ተኮር ሥራዎች እና የክልሉን የመልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑም ተመላክቷል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በ2018 በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ሥራ ላይ ላዋለው ከ39 ነጥብ 1ቢሊዮን ብር በላይ የተጨማሪ በጀት አጽድቋል።
#አሚኮ #AmharaRegionalState #Ethiopia🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
- የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
