🚫 ለሥልጣን ጥመኞች የሚከፈለው መስዋዕትነት እስከ መቼ

24

 

ሕገ ወጡ ሕወሃት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በግጭት፣ በጦርነት እና በጥፋት ተግባራት የታወቀ ቡድን ነው። በተለይም ከሥልጣን ከተባረረ በኋላ የውጭ ጠላቶች የጥፋት አስፈጻሚ በመኾን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በከፈተው ጦርነት በርካታ ቀውሶችን ማስከተሉ ከትውልድ ትውልድ የማይረሳ የገሀዱ ዓለም ዕውነታ ነው።

​ሕገወጥ ቡድኑ በሥልጣን ቆይታው ውስጥ በርካታ ሀብት ዘርፏል፣ አውድሟል፣ እንዲሁም እጅግ ብዙ የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ኾኗል። ወጣቶችን ያለ ርህራሄ ለጦርነት በመማገድ የእሳት ሲሳይ አድርጓቸዋል። እናቶች የልጆቻቸውን መከራ በሆዳቸው ተሸክመው በስቃይ እንዲኖሩ መገደዳቸው እና በየቤቱ የደረሰው ሰቆቃ በቃላት የሚገለጽ አይደለም።

​በተለይም በአማራ ክልል ወልቃይት እና በሌሎች አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሰወረ አይደለም። ቡድኑ ከሰብዓዊነት ባህሪው ሙሉ በሙሉ በመውጣት፣ የጠላትን ፍላጎት በማስፈጸም ሀገሪቱን የቀውስ ቀጣና ለማድረግ አሁንም ድረስ የሚታትር መኾኑ ተረጋግጧል።

ሕገ ወጥ ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ለፖለቲካ ሥልጣን ጥማቱ እና ለወንጀል ድርጊቶቹ መሸሸጊያ በማድረግ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈፀመበት ነው።

አሁንም እኩይ ባሕሪው አልለቀው ብሎ በትግራይ ክልል ውስጥ የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ፣ የቡድኑን አሠራር የሚቃወሙ እና ሰላም የሚሹ ሰዎችን በግልጽም ኾነ በስውር የማሳደድ፣ የማሰር እና የጅምላ ጭቆና ሰለባ እያደረገ ይገኛል።

የትግራይ ወጣት ተወልዶ ባደገበት ቀዬ እንደ ሌባ እና ዘራፊ እየተፈረጀበት ይገኛል። በገዛ ቀየው ባይተዋር ኾኖ ሀገሩን እንዲጠላ እና እንዲረሳ የሚገፋፋ አስከፊ ሁኔታ ተጋርጦበታል።
​ይህም ወጣቱ “ምነው ባልተወለድኩ!” እስከማለት እንዲጸጸት እያደረገው ነው።

​ዛሬ ላይ ወጣቱን ዳግመኛ ለጦርነት ሲሳይ የማድረግ ሴራ በትግራይ እናቶች ላይ የቀን ጨለማን አጥልቷል። የልጆቻቸውን ሕይወት እንደ ቅጠል የማርገፍ ታላቅ ስቃይ እና ስጋት ፈጥሯል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ሕገ ወጥ ቡድኑ ከሥልጣን ውጭ መኖር እችላለሁ ብሎ የማያምን፣ የወረደ ዕለት የሚጠየቅበት ብዙ ወንጀልም የፈጸመ አሁንም በተለያየ የኢኮኖሚ ወንጀሎች፣ የሰባዊ መብት ጥሰቶች ብቻ አይደለም፣ በወርቅ እና በኮንትሮባንድ ንግድ እየተሳተፈ ያለ ቡድን ነው ይላሉ።

ስለዚህ ቡድኑ ሥልጣን ካላገኘ እጠየቃለሁ ብሎ ስለሚገምት የራሱን ህልውና ከትግራይ ሕዝብ ህልውና በላይ አድርጎ የሚወስድ ሕገ ወጥ ቡድን ነው ብለዋል።

ይህንን አሠራር የትግራይ ሕዝብ እና ወጣት አይፈልገውምም ብለዋል። አሁንም ሕዝቡ ሰላሙን ነው የሚፈልገው ነው ያሉት። የትግራይ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ሊባል በሚችል ደረጃ የሰላም ስምምነቱ ደጋፊ እንደኾነም ጠቁመዋል።

ነገር ግን የሰላም ስምምነቱ ጥቅሜን አደጋ ላይ ይጥላል ብሎ ያሰበ የወንጀለኞች ሥብሥብ ቡድን ግን አሁንም ወጣቱን እያሳደደ በሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ ካላስገባሁ እያለ እያቅራራ የሚሰማበት ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል። ይህ ተግባር ወንጀል መኾኑ ሊሰመርበት ይገባልም ነው ያሉት።

የሥልጣን ጥማት የጋረደው ሕገወጡ የሕወሃት ቡድን የትግራይ ወጣትን በአቋራጭ ሥልጣን የመጨበጫ እና የወንጀል መደበቂያ እያደረገ ነው። ሕገ ወጥ ቡድኑ ለራሱ ህልውና ሲል የማይዘው እና የማይጨብጠው ነገር እንደሌለም አብራርተዋል። ይህ ቡድን ወጣቱን እያፈነ ለሱዳን ጦርነት እየሸጠ ነውም ብለዋል።

የቡድኑ ህልውና እስከቀጠለ ድረስ የትግራይ ሕዝብ ለስቃይ እንደሚዳረግም ጠቁመዋል።
ይህን ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር ያለውን ጥምረት መነጠል ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) ሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ከምሥረታው ጀምሮ አማራን በጠላትነት ፈርጆ መነሳቱን ታሪክ ያስረዳል ብለዋል። የአማራን ለም መሬቶች ለመጠቀም ባለው ፍላጎት ባለፉት 30 ዓመታት ስጋት ይኾኑብኛል ያላቸውን ሲያጠፋ እና ሲያንገላታ መቆዬቱን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በአማራ ሕዝብ ላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በወታደራዊ እና በሌሎችም መስኮች ከፍተኛ በደል እንደፈጸመ እና የአማራን ሕልውና ለመፈታተን ጥረት እያደረገ የሚገኝ ሕገ ወጥ ቡድን ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

የሕገወጡ የሕወሃት ቡድንን በአንድነት ድርጊቱን ማውገዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የሕገወጥ ቡድኑን የሥልጣን ጥማት አጥብቆ መታገል ከመላ ኢትዮጵያውያን እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።

​አሚኮ #ኢትዮጵያ #ሰላም

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየመምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተሠራ ነው።