
ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ እና ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባሕል፣ የሃይማኖት እና የሰው ሀብት ባለቤት የኾነችው ሀገራችን ለረጅም ዓመታት በውጭ እና በውስጥ ኀይሎች የተዛነፉ ፍላጎቶች፣ በመዋቅራዊ ሕመሞች እና በግጭት አዙሪት ስትታወክ ቆይታለች። የዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መነሻዎች ከውጭ ጠላቶች አልያም ከራሳችን አለማወቅ የሚመነጩ ቢኾንም ችግሩን የባሰ አስከፊ ያደረገው ግን በእኛው መካከል ተዛምቶ ለሰቀቀን፣ ለርሃብ፣ ለስደት እና ለመገዳደል መዳረጉ ነው።
ይሁን እንጂ ከብዙ ዓመታት መታመም በኋላ አሁን የበሽታው ትክክለኛ ፈውስ መገኘቱን የሚያበስረው ክስተት ተፈጥሯል። ይኸውም አካታች የሀገረ መንግሥት ግንባታን መተግበር እና ማስቀጠል ነው። በዚህ መንገድ ላይ የቆዩ መሠረታዊ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ስብራቶች፣ አለመግባባቶች እና ግጭቶች በውይይት ዘላቂ እልባት ያገኙ ዘንድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ነው። ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንሥቶ በፍጹም ገለልተኝነት እና ሕዝብን መሥሎ በመቆም በርካታ የቅድመ ዝግጅት እና የሕዝብ ተሳትፎ ተግባራትን አከናውኗል።
የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ከላይ ወደ ታች በመንግሥት ወይም በፖለቲከኞች የተጫነ ሳይኾን ከቀበሌ ጀምሮ እያንዳንዱን ዜጋ ባሳተፈ መልኩ ከሕዝብ የተገኘ የዕውነተኛ ሃሳቦች ነጸብራቅ ነው። ኮሚሽኑ ሁሉንም አካታች የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ለመከተል ሰፊ ርቀቶችን ተጉዟል።
በሂደቱም ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ መምህራን እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች በቀጥታ ተሳትፈዋል።
በአካል መገኘት ላልቻሉ ዜጎች በድረ-ገጽ፣ በልዩ መተግበሪያዎች እና በፖስታ ሳጥኖች ሀሳባቸውን እንዲልኩ ምቹ ሁኔታዎችም ተፈጥረዋል።
በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበይነመረብ እና በአካል በመገኘት የየበኩላቸውን አበርክተዋል።
በሀገሪቱ የነበረውን የፖለቲካ አለመተማመን ለመቅረፍ ኮሚሽኑ ሁሉንም የፖለቲካ ኀይሎች ለማነጋገር ሰፊ የውይይት ሥራዎችን ሠርቷል።
እነዚህ ጥረቶች ተደርገው ከተሠበሠቡት ሃሳቦች መካከል የተገኙት ርዕሰ ጉዳዮች ተጠንተው ወደ ስምንት ዋና ዋና የትውልድ ተሻጋሪ አጀንዳዎች ተደራጅተው ለምክክር ይፋ ተደርገዋል። አጀንዳዎቹም የማንኛውንም ልዩ ቡድን ወይም ወገን ፍላጎት ብቻ የሚያንጸባርቁ ሳይኾኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የህልውና፣ የሰላም እና የወደፊት እጣ ፈንታ ስጋቶች እና ተስፋዎች የያዙ የጋራ ሀብቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክሩ ከኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመናት ታሪክ፣ ቁስል፣ ሕመም እና ተስፋ የተወለደ ነው። ከውጭ ያልተቀዳ፣ የኢትዮጵያውያንን ብስለት የሚያሳይ እና ልዩነትን በነፍጥ እና በግጭት ከመፍታት አዙሪት በመላቀቅ በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ድፍረት የተሞላበት ውሳኔም ነው።
ሂደቱ ሲጠናቀቅም በሕዝብ እና በሕዝብ፣ በሕዝብ እና በመንግሥት እንዲሁም በሕዝብ እና በተቋማት መካከል ዕምነት እንዲገነባ እና የመደማመጥ ባሕል እንዲጎለብት ያደርጋል።
የተከባበረች ሀገር መፍጠር፡ ኢትዮጵያውያን የተስማሙባት፣ የሚደማመጡባት፣ ስለነገዋ የጋራ ግንዛቤ የተያዘባት እና ሰላም የሰፈነባት አገር በልጆቿ እጅ ትሠራለች።
በግጭት እና በጦርነት የተጎዱ መልካም ኢትዮጵያዊ እሴቶች ከወደቁበት ይነሳሉ።
አሁን ላይ ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን በአንድ ታላቅ መድረክ ዙሪያ ተሠባሥበው ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እያካሄዱ ይገኛሉ። ይህ ታሪካዊ መድረክ የትላንት ቁስሎችን አክሞ፣ የዛሬን ልዩነቶች አቻችሎ፣ ለትውልድ የሚተርፍ ፍትሕ እና እኩልነት የሰፈነባት ሀገርን ለመገንባት የተዘረጋ ታላቅ ድልድይ ነው። ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል በተግባር እየታየበት ያለ በመኾኑ መላው ኢትዮጵያዊ በጋራ አጀንዳዎቹ ላይ መክሮ በአንድነት የሚቆምበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየተጻፈ ይገኛል።
#አሚኮ #ሀገራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
