
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቆይታቸውም የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ የለውጥ ታሪክ ውስጥ ስላለው ጉልህ ሚና በዝርዝር አስረድተዋል።
በ1966፣ በ1983 እና በ2010 ዓ.ም በተደረጉት ሀገራዊ የለውጥ ትግሎች ውስጥ የአማራ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲመጣ ግንባር ቀደም ሚና እንደነበረው አውስተዋል። በተለይም የ2010ሩ ለውጥ ሲመጣ መላው ሕዝብ በከፍተኛ ተስፋ ሀገርን የማጽናት ሕልም በደስታ እንደተቀበለው ገልጸዋል።
ከለውጡ በፊት የነበረውን የታፈነና የተዘጋ የፖለቲካ ሥርዓት ለረጅም ጊዜ እንደተዘጋ ቤት በመመሰል ለውጡ ሲመጣ ቤቱን በማናፈስ ንጹሕ አየር (የፖለቲካ መከፈት) እንዲገባ መደረጉን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የተዘጋን ቤት ለማናፈስ መስኮት ሲከፈት ከንጹሕ አየር ጋር አብረው እንደሚገቡ ‘ቢንቢዎች’፤ በፖለቲካው መከፈትም ምክንያት አጋጣሚውን በመጠቀም ጩኸት በመፍጠር ረብሻ የሚያነሱ ብሎም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከሚጻረሩ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ የሀገርን ህልውና የሚፈታተኑ ኃይሎች ብቅ ማለታቸውን አብራርተዋል። እነዚህ ኃይሎች በፈጠሩት ሁከት መነሻነት በሕዝቡ ዘንድ የነበረው ብሩህ ተስፋ ለጊዜው ወደ ስጋት ተቀይሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ እውነታው እየተገለጠ ሲመጣ ሕዝቡ ይህንን አፍራሽ መንፈስ በመገንዘብ የመደመር መንገድ ብቸኛው ሀገርን የማዳን አማራጭ መኾኑን መገንዘቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
#አሚኮ #ወቅታዊ_ጉዳይ #ጠቅላይ_ሚኒስትር_ዐቢይ_አሕመድ #ባሕር_ዳር #ኢትዮጵያ #AMECO #PMABIYAHMED #PMAbiy #AmharaMediaCorporation #Ethiopia #BahirDar #CurrentNews
ስማቸው አጥናፍ
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
