
የኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ሲፈተሽ ደጋግሞ የሚታየው አንዱ አስደናቂ ጉዳይ ማኅበረ-ልቦናዊ ዕውነት በውስጣዊ ልዩነቶች እና የሥልጣን ሽኩቻዎች መከፋፈል ቢኖርም የውጭ ጠላት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ሊዳፈር ሲመጣ ልዩነትን ወደ ጎን ትቶ በአንድነት የመነሳት የዘመናት ልማድ ነው። በዘመነ መሳፍንት ወቅት ሀገሪቱ በየአካባቢው በነበሩ መሳፍንት ተከፋፍላ እና ተዳክማ በነበረችበት የጨለማ ዘመን እንኳ የውጭ ወራሪዎች ድንበር ጥሰው ሲገቡ የውስጥ ጠባቸውን አቆይተው በጋራ ጠላታቸው ላይ በአንድነት ዘምተዋል።
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ያረጋገጡትም የዘመነ መሳፍንትን መከፋፈል ተከትሎ የመጣው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የውስጥ ፖለቲካዊ ሽኩቻቸውን ለሀገር ህልውና ሲሉ እንዴት ማሸጋገር እንደሚችሉ ጥልቅ ማሳያ መኾኑን ነው። ይህ በደማችን ውስጥ ያለው የሀገር ፍቅር ስሜት ኢትዮጵያውያን የቱንም ያህል በውስጥ ጉዳያቸው ቢወዛገቡም ለሀገራቸው ህልውና ሲባል ግን ማንኛውንም መስዋዕትነት በጋራ ለመክፈል ወደኋላ እንደማይሉ ሕያው ምስክር ነው።
ይህ የጋራ አንድነት እና ሀገርን የማስቀደም እሴት እጅግ ደምቆ የታየው በአጼ ምኒልክ ዘመን በተመዘገበው የዓድዋ ድል ላይ ነው። የጣሊያን ወራሪ ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመግፈፍ ሲመጣ አጼ ምኒልክ የክተት አዋጅ ሲያውጁ ኢትዮጵያውያን በቋንቋ፣ በሃይማኖት እና በአካባቢ ሳይከፋፈሉ ከዳር እስከ ዳር ” ሆ! ብለው በመነሳት በዓድዋ ተራሮች ላይ ወደር የሌለው ጀግንነት ፈጽመዋል።
ያ የጥቁር ሕዝቦች የኩራት ምንጭ የኾነው ድል የተገኘው አባቶቻችን እና እናቶቻችን የነበሩባቸውን የውስጥ ቅሬታዎች እና ልዩነቶች ለጊዜውም ቢኾን አሸጋግረው ለሀገራቸው ክብር በአንድ ልብ በመቆማቸው ነው። ጀግኖቹ አባቶቻችን በጦር ሜዳ ጠላትን ድል እንዳደረጉት ሁሉ ያ የጋራ የመቆም መንፈስ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እንደ ብሩህ ተስፋ ሲያበራ ይኖራል።
ዛሬ ላይ ይህንን ታሪካዊ የአንድነት መንፈስ ይዘን ወደ አሁኑ ዘመን ስንመጣ ኢትዮጵያውያን የገጠማቸውን የዘመናት የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ልዩነት ቁርሾ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት በሀገራዊ ምክክር ጥላ ስር ተሠባሥበዋል። የዘመናችን “የክተት አዋጅ” የጦርነት ሳይኾን ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር የመፍታት የሰላም ጥሪ ነው።
ቀደምት አባቶቻችን የውጭ ጠላትን ለመመከት በአንድነት እንደዘመቱት ሁሉ የዛሬው ትውልድም ሀገርን ከሚያፈርስ የውስጥ መከፋፈል እና ጥላቻ ራሱን ለማዳን ሀገርን አስቀድሞ በአንድ ቤተሰባዊ ጉባኤ ላይ ተቀምጧል። ይህ ሀገራዊ ምክክር የዘመነ መሳፍንትን የመከፋፈል አዙሪት በዘላቂነት ለመስበር እና የዓድዋን የድል መንፈስ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት መጭው ትውልድ ደም በማያፋስስ እና መቻቻል በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ እንዲኖር የሚያስችል ታሪካዊ የሽግግር ድልድይ ነው።
አባቶቻችን የውጭ ጠላትን በጋራ ክንድ እንዳንበረከኩት ሁሉ የዛሬው ትውልድ ደግሞ የውስጥ ልዩነቱን በሰላም በጠረጴዛ ለማሸነፍ ተቀምጧል።
የያኔውን አሸናፊነት ዛሬም በሰላም ግንባታ ለመድገም ውይይቶች ከስሜት እና ከፖለቲካ ትኩሳት ነጻ ኾነው በዕውቀት እና በማስረጃ ላይ ተመስርተው እንዲካሄዱ መትጋት ይገባል። የታሪክ ምሁራንም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ርቀው ዕውነታውን በሐቀኝነት መመርመር አለባቸው።
ማኅበረሰቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሁሉም አካላት የዓድዋ ድልን የአንድነት መንፈስ ሊደግሙት ይገባል። ይህ ሲኾን ሀገራዊ ምክክሩ የነገው ትውልድ በኩራት የሚዘክረው የጋራ ታሪካዊ ድላችን ይኾናል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
