የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎውን እያካሄደ ነው። በዛሬው የጉባኤ መርሐ ግብር የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርትን ለምክር ቤቱ አቅርቧል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በፍርድ ቤቶች ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል። ፕሬዝዳንቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳነሱት፦

የዳኝነት ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እንዲኹም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ሥነ ምግባርን ለማሻሻል የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የሕግ ማዕቀፎችን በማጽደቅ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል።

ብቃት ያላቸው የዳኝነት እና የፍትሕ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንዲኹም ጥናት እና ምርምር ለማድረግ የሚያስችል የሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት እንደገና በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱንም አንስተዋል።

የዳኝነት አገልግሎትን ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጭ ቆጣቢ እና ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የዳኝነት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ በባሕር ዳር፣ በደሴ፣ በጎንደር፣ በደብረ ብርሃን እና በደብረ ማርቆስ ምድብ ችሎቶች 17 ሺህ 460 ጉዳዮች ቀርበው ለ15 ሺህ 630 መዛግብት እልባት ተሰጥቷል ብለዋል።

በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች 49 ሺህ 341 ጉዳዮች ቀርበው ለ42 ሺህ 479 መዛግብት እልባት የተሰጠባቸው መኾኑን አብራርተዋል።

በወረዳ ፍርድ ቤቶች 444ሺህ 498 ጉዳዮች ቀርበው ለ424 ሺህ 847 መዛግብት እልባት ተሰጥቷል።

የብዝኀ ፍትሕ መስጫ ሥርዓቶችን ከማጠናከር አንጻር የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓትን በማጠናከር እና የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አቅማቸውን በማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ ስለመሠራቱም ተመላክቷል።

የባሕል ፍርድ ቤቶችን በ1ሺህ 377 ቀበሌዎች በማቋቋም ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል። ከግንቦት 2018 ዓ.ም ጀምሮ 2ሺህ 416 ባለጉዳዮች አገልግሎት እንዲያገኙም ተደርጓል ብለዋል። በዚህም በመደበኛው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ቢታይ ሊወጣ የነበረ ከ29 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማዳን እንደተቻለ አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል በባሕር ዳር ከተማ ለማቋቋም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋልም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።

በ25 ሄክታር መሬት ላይ ደረጃውን የጠበቀ የፍትሕ ማዕከል ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ገልጸዋል።

ለከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም ደረጃቸውን የጠበቁ ሕንጻዎች በመገንባት ላይ መኾኑን ጠቁመው አፈጻጸማቸውም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በየደረጃው ከሚገኙ ፍርድ ቤቶች ከዳኝነት ክፍያ እና ከመቀጫ ከ509 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል።