
አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ጋር በጋ እስከ ክረምት ለፍሬ የሚታገሉት አንድም ለዕለት ጉርስ፣ ሁለትም ልጆቻቸው ብዕር ጨብጠው የዓለምን ምስጢር እንዲመረምሩ እና ከድህነት አዙሪት እንዲወጡ ለማድረግ ነው።
በአርሶ አደሮች ቀየ የአንድ ሰው ጉልበት መተኪያ የሌለው ከፍተኛ ሃብት ነው። አንድ ልጅ ትምህርት ቤት ሲላክ ማሣ ላይ የአንድ ሰው ጉልበት ይጎድላል። ያንን ሃብት አሳልፎ ለትምህርት መስጠት የዕለት ርሃብን ፈቅዶ የነገን ብርሃን የመጠበቅ ያህል ታላቅ መስዋዕትነት ነው።
አርሶ አደሩ በባዶ እግሩ እየዳኸ፤ ራሱ ልብስ ሳይቀይር እና ፊደል ሳይቆጥር የትምህርትን ዋጋ ግን ከማንም በላይ ጠንቅቆ ይረዳል። ለልጆቹ ደብተር እና አልባሳት ለመግዛት የወተት ላሙን እና የእርሻ በሬውን ለገበያ ያወጣል። ይህ ያልተነገረለት፤ ኒሻን ያልተበረከተለት ሀገርን የመገንባት ታላቅ ሕዝባዊ ተጋድሎ ነው።
በደቡብ ጎንደር የእብናት ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ሉሌ ተኮላ የዚህ እውነተኛ ተጋድሎ ሕያው ማሳያ ናቸው። አቶ ሉሌ ተኮላ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 579 ነጥብ 99 ውጤት ያስመዘገበው የተማሪ ተመሥገን ሉሌ ወላጅ አባት ናቸው።
ልጃቸው ተመሥገን ገና በልጅነቱ ለትምህርት መፈጠሩን የተገነዘቡት አቶ ሉሌ ከታች ጀምሮ ለትምህርቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያድግ አድርገውታል።
11ኛ ክፍል ሲደርስም የገጠሩ ሕይወት እና የትምህርት መሠረተ ልማት እጥረት ብሩህ አዕምሮውን እንዳያደበዝዘው በመስጋት ከገጠር ወደ ደብረ ታቦር ከተማ በመላክ በግል ትምህርት ቤት በየወሩ ገንዘብ እየከፈሉ ትምህርቱን እንዲከታተል ማድረጋቸውን አጫውተውናል።
ልጃቸው ተመሥገን በሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተናው 579 ነጥብ 99 በማምጣት በሚኖሩበት ደቡብ ጎንደር ዞን አንደኛ፣ በአማራ ክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከከፍተኛዎቹ መካከል አንዱ በመኾኑ አኩርቷቸዋል።
ጀግናው አርሶ አደር አቶ ሉሌ ተኮላም በኩራት ተሞልተው “ልጄን በአርሶ አደር አቅም በግል ትምህርት ቤት እየከፈልኩ ያስተማርኩት ባለው አቅም ስለምተማመንበት ነው። ልጄ ከእኛ አልፎ ሀገር የሚጠብቅም የሀገር ኩራት ነው” በማለትም ያ በድካም የወረደው ላባቸው እና የከፈሉት መስዋዕትነት ሁሉ ፍሬ አፍርቶ በደስታ ዕንባ ተክሷል።
አቶ ሉሌ “አባቴ አቶ ተኮላ በ1990ዎቹ ልጆቹን በሙሉ ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምሳሌ ነበር። እኔም አርሶ አደር ብኾንም እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምሬአለሁ። ከአባቴ በወረስኩት ልምድ ነው ልጆቼን እያስተማርኩ ያለሁት” ብለዋል።
ይሁንና ይህ ታሪክ ውስን ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የሚያጣጥሙት የሕይወት ስኬት ነው። በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ራሳቸው ሳይማሩ በተመሳሳይ ፅናት እና ጥንካሬ ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ነገር ግን ልክ እንደ ተመሥገን የቤተሰባቸውን ድካም ተረድተው ወላጆቻቸውን የሚያኮሩት ልጆች ውስን ናቸው።
ብዙዎቹ ወጣቶች በከተማ ሕይወት ማዕበል ተማርከው፣ የመጡበትን አሻራ ዘንግተው አለያም በትዕግሥት ማጣት መስመራቸውን ስተው የወላጆቻቸውን ተስፋ ሲያጨልሙ ይታያሉ። በዚህ ጊዜ በልጁ ላይ የዘራው ቀለም ፍሬ አልባ ኾኖ ሲቀር የሚሰማው ሀዘን ጥልቅ ይኾናል።
ስለዚህም ነው በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎች ቆም ብለው ማሰብ ያለባቸው። እንደ ባለብሩህ አእምሮው ተማሪ ተመሥገን ሉሌ ሁሉ ከአርሶ አደር እና ከደሃ ቤት የወጣ ተማሪ ሁሉ የአንድ ቤተሰብ ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን የሙሉ ማኅበረሰብ አደራ በትከሻው ላይ እንዳለ ለአፍታ ሳይዘነጉ በትምህርት መጠንከር ይገባቸዋል።
ማንኛውም ተማሪ ፈተናዎችን ሁሉ ተቋቁሞ፤ ጊዜውን በዕቅድ መርቶ እና ራሱን ለታላቅ ዓላማ አዘጋጅቶ የቤተሰቡን አደራ መወጣት አለበት። ተመሥገን ሉሌ ይህንን አሳይቷል። በሀገር አቀፍ ፈተናው ያስመዘገበው ውጤት እና የወደፊት የሶፍትዌር ምሕንድስና ራዕዩም የዚህ ማረጋገጫ ነው።
አርሶ አደሩ የሚዘራውን የቀለም እርሻ በታላቅ ስኬት ለማጨድ አሁን ተራው የቀጣዮቹ ተማሪዎች ነው።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
