የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎውን ቀጥሏል። በጉባኤው የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ለምክር ቤቱ አቅርቧል።
የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አማረ ብርሃኑ (ዶ.ር) በሪፖርታቸው እንደገለጹት መሥሪያ ቤቱ የኦዲት አገልግሎቱን ተደራሽነት፣ ጥራት እና ውጤታማነት ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል።
ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው እንደገለጹት:-

በበጀት ዓመቱ 56 የፋይናንስ እና ሕጋዊነት ኦዲት ቡድኖችን እና አንድ የተጠቃለለ የኦዲት ቡድን በማደራጀት 241 ተቋማትን ኦዲት ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከጠቅላላው የክልሉ ዓመታዊ በጀት ውስጥ 40 ነጥብ 7 በመቶ የሚኾነውን ኦዲት ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ክልሉ ከሚሠበሠበው ገቢ 30 ነጥብ 9 በመቶ የሚኾነውን ኦዲት ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

ሂሳባቸው ኦዲት ተደርጎ የኦዲት አስተያየት ከተሰጣቸው 190 ተቋማት መካከል ነቀፌታ የሌለው ወይም ንጹህ የኦዲት አስተያየት ያገኙ 19 መሥሪያ ቤቶች መኾናቸውን ዋና ኦዲተሩ አብራርተዋል።

የኦዲት ጥራት ቁጥጥር ሥራዎች በተቋሙ የኦዲት ድጋፍ እና ክትትል ሥርዓት መሠረት እየተፈጸመ ስለመኾኑም ገልጸዋል።

የኦዲት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር የኦዲት ሥራዎች ከዓለም አቀፍ የኦዲት ደረጃዎች እና ከተቋሙ ማንዋሎች ጋር የተጣጣሙ ስለመኾናቸውም ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኦዲት ውጤታማነትን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው ልዩ ልዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተሠርቷል ነው ያሉት።

የባለሙያዎችን አቅም በሥልጠና በማሳደግ፣ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን በማከናዎን፣ የወረቀት አልባ አሠራርን መከተል እና የባለ ብዙ ዘርፍ ተግባራትን አካትቶ በመተግበር ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ዋና ኦዲተሩ አብራርተዋል።