
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ክላውድ ደኅንነት (Cloud Security) ማለት በበይነመረብ ላይ በተዘረጉ የኮምፒውተር መረቦች እና የመረጃ መሠረተ ልማቶች ውስጥ ያሉ መረጃዎችን፣ መተግበሪያዎችን እና ሥርዓቶችን ከሥርቆት፣ ከጥቃት እና ከግላዊነት መጣስ ለመጠበቅ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ፣ የፖሊሲ እና የቁጥጥር ሥልቶችን ያቀፈ እንደኾነ “IBM” የተባለው የቴክኖሎጂ እና የኮምፒውተር ኩባንያ መረጃ ያሳያል።
ትርጉሙ ሰፋ ተደርጎ ሲታይ አንድ ተቋም መረጃዎቹን በራሱ ኮምፒውተር ወይም ሰርቨር ከመያዝ ይልቅ ከርቀት በበይነመረብ ከተሳሰሩ ግዙፍ የመረጃ ቋቶች ላይ ማስቀመጥ የሚችልበት፣ የመረጃ ባለቤትነትን ጠብቆ የሚዘልቅበት፣ ቁጥጥር እና የጥበቃ ኃላፊነት እንዴት መወሰድ እንዳለበት የሚደነግግ የደኅንነት ሥርዓት ነው።
መረጃው በቅርብ ባሉ ኮምፒውተሮች ላይ ባይኖርም እንኳን በበይነመረብ በተሳሰረ ሥርዓት በእጅ እንዳለ ያህል ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ የተመሰጠረ እና ለባለቤቱ ብቻ በማንኛውም ሰዓት ተደራሽ እንዲኾን የሚያደርግ ዲጂታል ጥበቃ እና ቁጥጥር ነው።
የክላውድ ደኅንነት ለምን ያስፈልጋል?
#ለተጋሩ የኃላፊነት ወሰኖች፦
የክላውድ አገልግሎት አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን መሠረተ ልማት ደኅንነት ቢጠብቁም በሲስተሙ ላይ የሚቀመጡ መረጃዎችን ማመስጠር እና መቆለፍ፣ መተግባሪያዎችን (Apps) እና የሥራ ሂደቶችን የመጠበቅ ዋና ኃላፊነት የደንበኞቹ የራሳቸው ነው።
ስለኾነም የክላውድ አገልግሎትን ከሚጠቀሙ ደንበኞች የደኅንነት ስልቶች ባለፈ በክላውድ መሠረተ ልማት ላይ ሊደረጉ የሚገባቸው የደኅንነት ሥርዓቶች በመኖራቸው የኀላፊነት ወሰን ኖሮት ጥበቃ ይደረጋል፡፡
#የመረጃ ማፈትለክ (Data Leaks) እና የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል፦
የሳይበር ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቁ በመምጣታቸው ተቋማትን ካልታሰቡ የመረጃ ማፈትለኮች እና የደኅንነት ሥጋቶች ለመጠበቅ።
#ከተጠያቂነት አደጋዎች ለመዳን፦
ደኅንነቱ ያልተጠበቀ የመረጃ አያያዝ በደንበኞች መረጃ ላይ አደጋ በማስከተል ተቋማትን ለከፍተኛ ሕጋዊ ተጠያቂነት እና ቅጣት ስለሚዳርግ።
#የተቋማትን የአገልግሎት ዘላቂነት ለማረጋገጥ፦
ያለአንዳች የደኅንነት ሥጋት እና እክል የዕለት ተዕለት የንግድ እና የምርት እንቅስቃሴዎችን በጥሩ ኹኔታ ለማስቀጠል።
#የደንበኞችን እምነት ለመጠበቅ፦
ተቋማት የሚያሥተዳድሯቸውን የተጠቃሚዎች እና የደንበኞች መረጃ በአስተማማኝ ኹኔታ በመጠበቅ እምነትን ለማጠናከር።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
