አብሮ የመሥራት ሳይኾን አብሮ የማጥፋት ጥምረት!

4
ሕገ ወጡ ሕወሃት ከውልደቱ ጀምሮ እስከ አሁን የሀገር ውስጥ ጽንፈኞችን በመፍጠር እና አጋር በማድረግ እንዲኹም ለውጭ ጠላቶች በመላላክ ሀገር ለማፍረስ የሚሠራ ቡድን ነው።
ሥልጣኑን በበላይነት ተቆጣጥሬ የሕዝብ ሃብት ካልዘረፍኩ ሀገር ትፍረስ የሚል አቋሙን ያልቀየረው ሕገ ወጡ ሕወሃት አሁንም ያረጀ ያፈጀ ስልቱን ለመጠቀም እየተውተፈተፈ ይገኛል። ቡድኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ እና የእሱን የጽንፈኝነት አጀንዳ ከወረሱ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመጣመር ለአይጥና ድመት ጥምረታቸውም የዳቦ ስም ቆርሶ እየሰጠ በመንቀሳቀስ ላይ መኾኑን ተጨባጭ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይሁን እና ይህ የሕገ ወጥ ቡድኑ አካሄድ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ አይደለም። ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊትም ኾነ በኋላ ከተለያዩ ኀይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ይታወቃል።
የቡድኑን የኋላ ታሪክ እና የአሁኑን አካሄድ አዋህዶ መፈተሽ ይህ ሕገ ወጥ ቡድን ተመልሶ ወደ ሥልጣን የመምጣት ዕድል ቢያገኝ ኢትዮጵያ፣ የአማራ እና ሌሎች ሕዝቦች እንዲኹም ጥምረት ፈጥረናል የሚሉ ቡድኖች ምን ዓይነት እጣ-ፈንታ እንደሚከተላቸው ግልጽ ማሳያ ይኾናል።
ሕገ ወጡ ሕወሃት ገና በጫካ ትግል ዘመኑ በትግራይ ክልል ብቸኛ የበላይ ተዋናይ ለመኾን ከእርሱ ጋር የርዕዮተ-ዓለም እና የስትራቴጂ ልዩነት የነበራቸውን ሌሎች የነጻነት ግንባሮች በኀይል ደምስሷል።
ለዚህ ማሳያዎቹ የትግራይ ነጻነት ግንባር፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ናቸው። ሕገ ወጡ ሕወሃት ገና በምሥረታው ዋዜማ ላይ እያለ ከድርጅቶቹ ጋር አብሮ ለመሥራት ተስማምቶ የነበረ ቢኾንም በኋላ ላይ ግን በድርድር ስም አመራሮቹን በምሽት በመግደል እና አባላቱን በመበተን ድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉ እንዳጠፋቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ደርግ በ1983 ዓ.ም ከተገረሰሰ በኋላ ሕገ ወጡ ሕወሃት የሽግግር መንግሥት ሲመሰርት አብረውት የነበሩ የነጻነት ግንባሮችን በማግለል በራሱ ቁጥጥር ሥር ያሉ ድርጅቶችን መተካቱም የሚታወስ ነው።
ሕገ ወጡ ሕወሃት እውነተኛ አጋር ድርጅቶችን ከማቅረብ ይልቅ ለማጥፋት የሚመቹትን እና በራሱ ቁጥጥር ሥር የሚውሉትን ቡድኖች ይመርጣል።
የቡድኑ አጋሮችን የማጥፋት የኋላ ታሪክ ከተቀናቃኞቹ አልፎ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ ባሉና በትግሉ ትልቅ አሻራ ባሳረፉ ሞጋች መሪዎች ላይ ጭምር ያረፈ ነበር።
እንደ ፖለቲካ ምሁራን ዕይታ አሁን ተመሠረተ የሚባለው ሕወሃት ራሱ የዳቦ ስም ቆርሶ የሰጠው ጥምረት በግብጽ እና ኤርትራ ድጋፍ የተመሠረተ እንደመኾኑ ዓለማው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማዳከም፣ የፌዴራል መዋቅሩን ከማናጋት እና በዋነኝነት ደግሞ የአማራን ሕዝብ ወሳኝ የሕልውና ጥያቄዎች ከማጨናገፍ ያለፈ ዓላማ የለውም።
ሕገ ወጡ ሕወሃት ገና ከጅምሩ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ የተነሳ ቡድን በመኾኑ አሁን የፈጠረው ጥምረት በክልሉ ውስጥ ቀውሶችን በመደገፍ እና በማባባስ ሕዝቡን በድህነት ውስጥ ለማኖር የተጠነሰሰ እኩይ ጥምረት ነውም ይላሉ።
በተለይም እንደ ግብጽ እና ኤርትራ ባሉ የውጭ ጠላቶች ድጋፍ የተመሠረተው ይህ ርባና ቢስ ጥምረት በዳግም የውክልና ጦርነት ትግራይን የጦር አውድማ የማድረግ ዓላማም አለው። ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ በመቀነስ የባሕር በር ጥያቄዋን ለማደናቀፍ የሚደረግ የውጭ ኀይሎች የረዥም ጊዜ የጥፋት አጀንዳ ማስፈጸሚያ መኾኑንም ምሁራኑ በጽኑ ያሰምሩበታል።
የታሪክ ዕውነታዎች እንደሚያሳዩት ሕገ ወጡ ሕወሃት ፍፁም እኩልነት ላይ የተመሠረተ ጥምረትን በባሕሪው አያውቅም፤ አያስተናግድምም።
ጥምረት የሚፈጥረው ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር የማዋል የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት ብቻ ነው። ዕድል ቀንቶት ዳግሞ የበላይነቱን መቆጣጠር ቢችል የፖለቲካ ርዕዮት-ዓለም ልዩነት ያላቸውን መሪዎች እና ተመሪዎች ከሀገር ማፍረስ እስከ ዘር ጭፍጨፋ ያለምንም ርህራሄ የሚፈጽም ሕገ ወጥ ቡድን ነው።
ቡድኑ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በተለይም በሰሜኑ ጦርነት የደረሰበትን የፖለቲካ እና የወታደራዊ ስብራት ለመካስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የኾነ የበቀል እርምጃ ይፈጽማል። የአማራ ሕዝብንም ዋነኛ ተጠቂ እንደሚያደርግም ሳይታለም የተፈታ ነው።
የታሪክ መዛግብት በግልጽ እንደሚያሳዩት ሕገ ወጡ ሕወሃት አብሮት ለታገለ፣ አብሮት ለደማና ሥልጣን ላይ እንዲወጣ ላገዘው አካል ታማኝ ኾኖ አያውቅም። የአሁኑ ጥምረትም ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚጠቀመው ፈረስ እንጅ እውነተኛ አጋርነት አይደለም።
ስለኾነም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በጫካ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ከሕገ ወጡ ሕወሃት የጥፋት አካሄድ ጋር ሲሰለፉ ከሕወሃት የጥፋት ወጥመድ በገዛ እጃቸው እየገቡ መኾኑን ማወቅ አለባቸው። ካለፈው የታሪክ ስህተት ተምረው እና ከመንግሥት ጎን ኾነው ሀገራዊ አንድነትን ከማስከበር ውጭ አማራጭ እንደሌለም ሊገነዘቡ ይገባል።
ኢትዮጵያ እድገት እና ደኅንነቷን ለማረጋገጥ ከሚያስችሏት ብሔራዊ ጥቅሞች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዋነኞቹ ናቸው።
የሕዳሴ ግድቡን በስኬት ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋንም በውጤታማነት እያስኬደች ትገኛለች። ይህን የተመለከቱት ግብጽ እና ኤርትራ ሀገሪቱን ከብሔራዊ ጥቅሟ ለማፋታት ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም። በእጅ አዙር የሀገር ውስጥ ታጣቂዎችን በማደራጀት እና በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማዳከም መሥራት ከጀመሩም ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ነገር ግን የጠላቶቿን ሴራ በጣጥሳ ሕዳሴውን ግድብ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ ወደቀች ሲሏት እየጠነከረች የያዘቻቸውን ግቦች ከዳር ማድረሷ አይቀሬ ኾኗል። አሁን የተፈጠሩትን ትናንሽ የውጭ ጠላት ፈረሶችን በተባበረ ክንድ አስወግዳ የያዘቻቸው የልማት እና የዕድገት ግቦችን ታሳካለች።
ኢትዮጵያ ወዳጅና ጠላቱን ለይቶ የሚያውቅ፤ ሁለተኛ ስህተት የማይሠራ የጠንካራ ሕዝብ ባለቤት መኾኗን በተግባር እንደምታረጋግጥም ታውቆ ያደረ ጉዳይ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን የፀጥታ ኹኔታ እና የሕግ የበላይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ሌተናል ጄነራል መሐመድ ተሰማ አረጋገጡ።