
አሮጌው ዓመት ተሰናብቶ አዲሱ ሲጠባ የሁሉም ልብ በብሩህ ተስፋ እና በበጎ ምኞት ይሞላል። ያለፈው ጊዜ በክፉም ኾነ በበጎ ቢጠናቀቅ አዲሱን ዓመት በጤና እና በሰላም ለመቀበል ከመመኘት ባሻገር በርካቶች የዕቅድ ሰሌዳቸውን አዲስ በተገዛ ማስታወሻ ላይ ያሰፍራሉ።
የተሻለ ማንነትን ለመገንባት፣ አዳዲስ ክህሎቶችን ለመማር፣ ጤናን ለመጠበቅ ወይም የገንዘብ አቅምን ለማሳደግ ቃል መግባት የተለመደ ነው። ይሁን እንጅ የዓመቱ መባቻ አልፎ ጥቂት ወራት ገፋ ሲል በታላቅ ጉጉት የተጀመሩ ዕቅዶች እንደ ጧት ጤዛ ሲረግፉ እና የግብ ክሽፈት የብዙዎች የጋራ ዕጣ ፈንታ ሲኾን ይስተዋላል። አብዛኛዎቹ የዕቅድ ዝግጅቶች በጊዜያዊ የስሜት መነሳሳት ላይ ብቻ የተመሠረቱ መኾናቸው ደግሞ ለክሽፈት ዋነኛው ምክንያት መኾኑን ምሁራን ያስረዳሉ። ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት መፍትሔ ይኾናሉ ያሏቸውን ሐሳቦችም አስቀምጠዋል።
ጀምስ ክሊር “አቶሚክ ሀቢት” በተሰኘው መጽሐፋቸው በአንድ ጀንበር ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ከመሞከር ይልቅ በየቀኑ በአንድ በመቶ መሻሻል ላይ ማተኮር እና የባሕሪ ወይም የማንነት ለውጥ ማምጣት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
ቻርልስ ዱሂግ “ዘ ፓወር ኦፍ ሃቢት” በተሰኘው መጽሐፋቸው መጥፎ ልማድን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም ብለው ያምናሉ። ቀስቃሽ፣ መደበኛ ድርጊት እና ሽልማት የተሰኘውን የልማድ ዑደት በመረዳት መጥፎ ድርጊቱን በሌላ ጠቃሚ ልማድ መተካት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲዋ ፕሮፌሰር ካሮል ድዌክ በበኩላቸው የዕድገት አስተሳሰብን ማዳበር ወሳኝ መኾኑን ያነሳሉ። ችሎታ ተፈጥሯዊ ነው ብለው የሚያምኑ እና ትንሽ መሰናክል ሲገጥማቸው ቶሎ ተስፋ የሚቆርጡ የተገደበ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አሉ። ማንኛውም ክህሎት በልምምድ እንደሚዳብር በማመን ዕቅድ ሲሰናከል ራስን ከመኮነን ይልቅ ስህተትን እንደ መማሪያ አጋጣሚ የሚወስዱ የዕድገት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አሉ ባይ ናቸው።
ችሎታ ተፈጥሯዊ ነው ከሚል የተገደበ አስተሳሰብ ወጥቶ ስህተትን እንደ መማሪያ በመውሰድ ማንኛውም ክህሎት በልምምድ እንደሚያድግ በማመን የዕድገት
አስተሳሰብን ማዳበር ይገባል በሚልም ይመክራሉ።
ቢ.ጄ ፎግ (ዶ.ር) በበኩላቸው የሰዎች መነሳሳት ተለዋዋጭ በመኾኑ አዳዲስ ተግባራትን እጅግ ቀላል ማድረግ እና ቀድሞ ካለን ጠንካራ ልማድ ጋር አያይዞ መተግበር ይገባል ሲሉ አስፍረዋል።
የፕሮፌሰር ኤድዊን ሎክ የግብ አቀማመጥ እና የተግባር አፈጻጸም ንድፈ ሀሳብ እንደሚያስረዳው ተግባራትን በምናከናውንበት ጊዜ ግቦችን አዕምሮን እንዲያነቃቁ እና ለሥራ እንዲያተጉ ግልጽ ብቻ ሳይኾኑ ፈታኝ እና አቅምን የሚጠይቁ መኾን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ስኬታማ የለውጥ ጉዞ የስሜት ጉዳይ ብቻ ሳይኾን እነዚህን ጥቃቅን ልማዶች እና ስትራቴጂካዊ የአስተሳሰብ ለውጦች አጣምሮ የመያዝ የሳይንስ ውጤት ነው። ታዲያ አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሊተካ ጫፍ ላይ እንገኛለንና የስንቶቻችን ዕቅዶች ሳይንሳዊ ይኾኑ? ስንቶቻችንስ በዕቅድ እንመራለን? ያለፉ ችግሮች እንደጤዛ ተራግፈው፤ መጭው አዲስ ዓመት ብሩህ እንዲኾን ከመመኘትም ባለፈ አቅደን ለመተግበር እንሥራ።
ምክረ ሐሳቦቻችሁን አጋሩን!
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
