ድንች – የብዙ ኢትዮጵያውያን የማዕድ ጌጥ

12
በአማራ ክልል ድንች በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካካል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ተጠቃሽ ነው። አርሶ አደር ተሥፋዬ እያሱም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ድንች ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዋና የምግብ ዋስትና ማስጠበቂያ ግንብ እና የገቢ ምንጭ መኾኑን ነግረውናል።
​በሚሰጠው የግብርና ሥልጠና ታግዞ በኩታገጠም፣ በረድፍ እና በተሻሻሉ ዘዴዎች በመዘራቱ አርሶ አደሮች አጥጋቢ ምርት እያገኙ መኾኑን ይናገራሉ ። ከጤፍ እና ከሌሎች ሰብሎች በተለየ መልኩ በወረዳው በዋናነት የሚመረተው ድንች፣ ለአርሶ አደሮች የኑሮ ማሻሻያ እና የቤት ውስጥ ወጪዎችን ለመሸፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንዳለው ያነሳሉ።
በአካባቢው ድንች በዓመት እስከ ሁለት ጊዜ የሚመረት መኮኑን የገለጹት አርሶ አደሩ የክረምት ድንች ምርት በማጠናቀቅ አሁን ላይ በመስከረም ወር የሚዘራውን ድንች ለማስጀመር ማሳዎቸውን አዘጋጅተዋል። ድንች ለአካባቢው ማኅበረሰብ ኑሮ ማስተካከያ ትልቅ ምሰሶ በመኾን ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የላቀ ድርሻ እየተጫወተ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ንጋቱ ዞኑ በድንች ምርት የሚታወቅ ሲኾን በመኸር እርሻ ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እየለማ ይገኛል ብለዋል።
​በስናን፣ ማቻከል፣ ጎዛምን፣ ሰዴ፣ ደባይ ጥላትን ግን እና ቢቡኝ ወረዳዎች በክላስተር እየተከናወነ ባለው በዚህ የልማት ሥራ የተሻሻሉ ሳይንሳዊ አሠራሮችን በመጠቀም በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት ለማግኘት እና ምርታማነቱን ለማሳደግ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
​ድንች በአጭር ጊዜ የሚደርስ፤ በትንሽ መሬት ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት እና የአርሶ አደሮችን ኑሮ ማሻሻያ በመኾን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው። ድንች የአሲዳማ መሬትን የመቋቋም እና የመሬት አጠቃቀምን የማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ተገልጿል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሆርቲ ካልቸር ልማትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አበበ መኮነን በክልሉ በመኸር ከ156 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በኩታ ገጠም እና በሌሎችም አሠራሮች እየተከናወነ በሚገኘው የድንች ልማት ሥራ ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በክልሉ በአምስት ዞኖች ደቡብ ጎንደር፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች ድንች በስፋት ይመረታል ያሉት ዳይሬክተሩ አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ምርቱ በመሠብሠብ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
​ይህ የድንች ልማት ሥራ የክልሉን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ ማዕከላት የሚቀርብ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ነው ብለዋል። ድንች በሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤት የሚዘወተር እና የዕለት ተዕለት የምግብ ሰንሰለት ቁልፍ አካል እንደኾነም ተመልክቷል።
ይህ ሰብል የማዕድ ጌጥ እና የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ ግንብ የኾነ ሰብል በተለያየ መልኩ ተዘጋጅቶ ገበታ ላይ ይቀርባል።
ለመኾኑ ድንች በየአካባቢያችሁ እንዴት ተዘጋጅቶ ነው ገበታ ላይ የሚቀርበው? አስተያየታችሁን በሀሳብ መስጫው ላይ አካፍሉን!
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የዛሬው ትጋቴ፤ የነገው ሀገር የማገልገል መሠረቴ ነው”
Next articleችግሮችን እንደጤዛ በማራገፉ በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ!