ለዓመታት ሞትን፤ ታገትን፤ በአዲሱ ዓመት ሰላምን ስጡን!

10
ወጣትነት የሕይወት ዘመን ስንቅ የሚያዝበት፤ የለውጥ መሠረት የሚገነባበት፤ ጉልበት ሳይደክም ሃብት ለመያዝ፤ ዓላማን ለማሳካት፤ ስኬትን ለመጎናጸፍ ትግል የሚደረግበት የሕይወት ወሳኝ ጊዜ ነው።
የአዲስ ዓመት ዋዜማ ደግሞ ለወጣቶች ልዩ ያደርገዋል። ወጣትነታችውን በስኬት ለማጀብ የሕይወት ዘመን መስመራቸውን የሚለዩበት፤ የለውጥ መንገድን የሚቀይሱበት፤ ፈተናን ተቋቁሞ ውጤታማ ለመኾን ብርታትን፤ ብልሃት እና ጥበብን ለመተግበር ዕቅድ የሚያወጡበት ጊዜ ነው።
ወጣቶች አዲስ ዓመትን በጉጉት ይጠብቋታል፤ ፈጣሪ ቢያሳካልኝ ብለው ራሳቸውን በሥራ ለመለወጥ ዕቅድ ያወጡባታል፤ ትዳር ለመመሥረት ለወላጆቻቸው ፍሬ ለማሳየት ይወጥኑባታል፤ በሥራቸው ውጤታማ በመኾን ወላጆቻቸውን ለማገዝ ያልሙባታል።
በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት ግን የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት እየፈተነ ይገኛል። ወጣቶች በከተማቸው እና ከከተማቸው ውጭ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል።
የሰላምን ጥቅም ያልተረዱ ደግሞ ሕገ ወጥ ታጣቂዎችን በመቀላቀል ጊዜ፣ ጉልበት እና የማይተካ ሕይወታቸውንም ገብረዋል። የሰላምን ጥቅም የተረዱ ግን ከተሳሳተ መንገድ በመውጣት የሰላምን አማራጭ ተቀብለዋል።
በአዲሱ ዓመት ወጣቶች ተስፋን ሰንቀዋል፤ ከአደይ አበባ ጋር ተስፋቸውን ተክለዋል፤ የዓመቷን የፍካት ጀምበር ከስኬታቸው ጋር አስተሳስረዋል፤ የመስከረምን የጠራ ሰማይ ተመልክተው ጥራት ያለው ሥራ፤ ስኬታማ ሕይወት፤ ያልተበረዘ ሀብት ለማልማት ወጥነዋል። ለስኬታቸውም ሰላምን ተማጽነዋል። ለዓመታት ሞትን፤ ታገትን፤ በአዲሱ ዓመት ሰላምን ስጡን ሲሉም ታጣቂዎችን እየለመኑ ነው።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ ወጣቶች የሰላም እጦት ወጣቶች ሕይወታቸውን እንዲያጡ፤ ተስፋ እንዲቆርጡ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳይኾኑ አድርጓል ብለዋል። ሠርተው ለመለወጥ የሚሞክሩ ወጣቶች በእገታ እና በጸጥታ ችግር ምክንያት ስደትን አማራጭ እንዲያደርጉ አስገድዷል ነው ያሉት። በጦርነት የሚሳተፉ፤ የሚታገቱ እና የችግሩ ገፈት ቀማሽም ወጣቶች መኾናቸውን ተናግረዋል።
የሀገር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የስኬት ዘርፎች የሚመዘገቡት በወጣቶች በመኾኑ ሰላምን በማጽናት ወጣቶችን የልማት አርበኛ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ሕገ ወጥ ታጣቂዎች እገታን የገቢ ምንጭ በማድረጋቸው ወጣቶች ለሥራ፤ ቤተሰብን ለመጠየቅ ከቦታ ቦታ በስጋት እንደሚቀሳቀሱ አድርጓል ነው ያሉት። በዚህም ወጣቶች ከሥራ እንዲርቁ፤ ለተለያዩ ሱሶች እንዲጋለጡ፤ ለሥነ ልቦና ችግር እንዲጋለጡ አድርጓል ብለዋል።
ግጭት የክልሉን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚገታ በመኾኑ የሰላምን መንገድ በመከተል፤ ሰላምን በማጽናት የወጣቶችን የነገ ተስፋ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
ወጣቶች አካባቢን በንቃት በመጠበቅ፤ የሰላም አርአያ በመኾን፤ የሰላምን አስፈላጊነት በማስተማር ለሰላም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አሳስበዋል።
#አሚኮ#ሰላም#ወጣቶች#ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር#ነሐሴ_24_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleችግሮችን እንደጤዛ በማራገፉ በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ!
Next articleከመሬት ሥር የተደበቀው ቢሊዮን ዶላር በአማራ ክልል