
የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ተሰማ ከዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ዞኑ ተስፋ የሚሰጥ የሰላም፣ የአቅም ግንባታ፣ የስምሪት፣ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የሕዝብ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የዞኑ መሪዎች ባደረጉት መራር ትግል ክልሉን እና ሀገርን ከመፍረስ የታደገ ሚና መጫወታቸውን አዛዡ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት የዞኑ መንግሥታዊ መዋቅር በላቀ ሁኔታ ተደራጅቶ ሕዝብን እያስተዳደረ ይገኛል። የዞን እና የወረዳ ፖሊስ፣ ሰላም አስከባሪ እና ሚሊሻ ተገንብቷል። ፅንፈኛው በፈፀማቸው ግፎች በሕዝብ ተተፍቷል።
ተላላኪው ፅንፈኛ አፍሮ እና ከየከተሞች ተባሯል፤ የሕዝብ ድጋፍ አጥቶ ተነጥሏል፤ ከመኪና ወርዶ እግረኛ ሆኗል። አሁን የቀረው ነገር ግብፅን፣ ሻዕቢያን እና ሕወሃትን የጡት አባት አድርጎ ላያድኑት የሙጥኝ ማለት ነው።
ሌተናል ጄነራል መሐመድ ተሰማ እንዳሉት ሕዝቡ ሰላም፣ ፍትሕ፣ ልማት እና መልካም አሥተዳደር እንደሚፈልግ አረጋግጧል። በአንዳንድ ቦታዎች ሕዝብ ፅንፈኛውን ብቻውን ገጥሞ ተዋግቷል። አመራሩን እና መከላከያን ይደግፋል። የተደራጀ መረጃም እየሰጠ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ በምርጫ እንዳይሳተፍ ፅንፈኞች “አትምረጥ” ብለው ቢያስፈራሩትም እየተተኮሰበትም ቢሆን ይበጀኛል ያለውን ፓርቲ በመምረጥ ለሰላም ያለውን ቀናዒነት አረጋግጧል ነው ያሉት። ይህ የዞኑ አመራር በሠራው የመጣ ትልቅ ውጤት ነው።
ምዕራብ ጎጃምን ዞን ከጥፋት መልዕክተኞች ለማፅዳት እየተወሰደ ባለው የፀረ ሽምቅ ኦፕሬሽን የተገኙትን ውጤቶች ይበልጥ ለማጎልበት የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ በዞኑ የሰላም እና የልማት ሥራዎች እየተጠናከሩ የመጡት ከሠራዊቱ ጋር በመቀናጀት በተደረገው ስምሪት መኾኑን ገልጸዋል። አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ የዞኑ አመራር ያልተቆጠበ ጥረት እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
ዘገባዉ የምስራቅ ዕዝ ነው።
#ባሕር ዳር ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
