
የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በጉባኤው ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንደገለጹት ከተሞችን በማዘመን እና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በከተሞች የመልካም አሥተዳደር ማረጋገጥ፣ መሠረተ ልማቶችን ማስፋት፣ ከተሞችን ጽዱ እና አረንጓዴ እንዲኾኑ ለማድረግ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በዚህም 214 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት። 96 ከተሞችም የመዘጋጃቤታዊ ስታንዳርድ እንዲኖራቸው ተደርጓል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
በከተሞች በቴክኖሎጂ የተደገፉ የገበያ ልማት ሥራዎች መሠራታቸውንም ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የገለጹት። በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አሰጣጥ፣ በሕጋዊነት እና ቁጥጥር እንዲኹም በመሠረታዊ ምርቶች አቅርቦት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ626 ሺህ በላይ የንግድ እና ገበያ አገልግሎቶችን በበየነ መረብ በመስጠት የአገልግሎት ፈላጊ ዜጎችን ጫና መቀነስ መቻሉን አብራርተዋል።
ከ101 ሺህ በላይ አዳዲስ የንግድ ምዝገባዎችን፣ እንዲኹም ከ140ሺህ በላይ አዲስ የንግድ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱንም አንስተዋል።
ሕጋዊነትን ለማስፈን ሰፊ የቁጥጥር እና የመሠረታዊ ምርቶች አቅርቦት ላይም ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ነው የተናገሩት። የሸቀጥ እና የመሠረታዊ ፍጆታ ምርቶች በስፋት መቅረባቸውም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
