
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ ዘላቂ የጤና መድኅን ሥርዓት በመገንባት የዜጎችን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉን አቀፍ ተደራሽነትን ለማስፋት በተደረገው ጥረትም አገልግሎቱ በ1ሺህ 279 ወረዳዎች መድረሱን እና በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከ 55 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መኾናቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በአገልግሎቱ ላይ ያጋጠመውን የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤቶችን በመክፈት እና ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በ2019 በጀት ዓመት ሽፋኑን ይበልጥ ለማስፋት ሁሉም አካላት እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ በበኩላቸው በክልሉ የጤና መድኅን ፕሮግራሙ ሰፊ ዕድገት በማሳየት 91 በመቶ የሚኾነውን የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ በበኩላቸው ጤና የሀገር ዕድገት መሠረት መኾኑን አንስተው የማኅበረሰቡን የጤና እክል በመቅረፍ ረገድ የጤና መድኅን አገልግሎቱ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም መርሐግብሩ ሲጀመር የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውት እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ማኅበረሰቡ የፕሮግራሙን አስፈላጊነት በመገንዘቡ የሕክምና እንግልቱ በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሳ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
