
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በ2018 ዓ.ም የኤክስፖርት ምርት፣ የውጭ ምርት መተካት እና ገበያ ማረጋጋትን በተመለከተ የተከናወኑ ሥራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ ባለፈው 2018 በጀት ዓመት በኤክስፖርት ምርቶች የተሻለ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን አመላክተዋል።
በእንሰሳት ግብይትም ባለፈው በጀት ዓመት 32 ሺህ 451 የሚኾኑ የቁም እንስሳትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።
ተኪ ምርት ግብዓት ማምረት ላይ ለዘይት ጥሬ ዕቃ አቅርቦት 1ነጥብ 5ሚሊዮን ኩንታል አኩሪ አተር ለፋብሪካዎች ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ከግብርና ምርት ከጥራጥሬ፣ ከቅባት እህሎች እና ከቡና 562 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ነው የገለጹት።
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና ጤናማ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት አዳዲስ እና ተጨባጭ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑንም አብራርተዋል። የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋት አምራቹን እና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ሲኾን “በአንድ ወረዳ አንድ የገበያ ማዕከል” እንዲኖር በማድረግ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም 42 ወረዳዎች የገበያ ማዕከሎቻቸውን አጠናቀው ወደ ግብይት የገቡ ሲኾን 35 ማዕከላት ደግሞ በመገንባት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በ 8 የሪጅኦ ፖሊታንት ከተሞች ሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ ሲኾን በሰባቱ የዞን መቀመጫ ከተሞችም ሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላት በመገንባት ላይ ናቸው ብለዋል።
አምራቹን እና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘቱ ሂደት አላስፈላጊ ደላላዎችን እና ተዋናዮችን በማስወገድ ረገድ ትልቅ ለውጥ ታይቷልም ብለዋል። በዚህም በሸማቾች ዘንድ ከ7 እስከ 22 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ እንዲኖር መደረጉን ነው የገለጹት።
በክልሉ ከእሁድ እስከ እሁድ ግብይት የሚፈጸምባቸው እና አምራች እና ሸማቾች በቀጥታ የሚገናኙባቸው 259 የሰንበት ገበያዎች በሥራ ላይ መኾናቸውንም ነው የገለጹት።
በተለይም ጎዳና ላይ ግብይት እንዲቀር በማድረግ ጤናማ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጽዱ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር ተደርጓል፤ እንዲሁም የግብይት ሕገ-ወጥነትን ለመቆጣጠርም ሢሠራ መቆየቱን አንስተዋል በመግለጫው።
ምቹ የገበያ ሰንሰለት በመዘርጋት ከድለላ ነፃ የኾነ የግብይት ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።
በቀጣይም ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ላይ ቁጥጥር በማድረግ በቅንጅት እረምጃ የሚወሰድ መኾኑን ነው የገለጹት።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
