በአማራ ክልል አምራችአምራች ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ከ789 ቶን በላይ ተኪ ምርቶች ተመርተዋል።

8
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በጉባኤው ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማስፋት እና ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በማዕድናት አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ደረጃን ማሻሻል ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
በ”ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ንቅናቄ ለ152 ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እና የኤሌክትሪክ ኀይል እንዲሟላላቸው መደረጉንም ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር 789 ነጥብ 9 ቶን ተኪ ምርቶችን ማምረት ተችሏልም ብለዋል። በዚህም ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደተቻለ አንስተዋል።
በግብርናው ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት በሄክታር በአማካኝ ከ28 ወደ 30 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በመኸር ወቅት በመደበኛ እና ለገበያ በተመረጡ ሰብሎች ከ188 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል ተሠብሥቧል ነው ያሉት።
የእርሻ ሜካናይዜሽን አጠቃቀምን በማሳደግ 976 ትራክተሮችን፣ 7 ሺህ 670 ሞተር ፖምፖችን እና ሌሎችንም የእርሻ ሜካናይዜሽን ግብዓቶችን ማቅረብ ተችሏልም ብለዋል።
በመስኖ እርሻ ከ481 ሺህ በላይ ሄክታር በማልማት ከ40 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ማምረት ተችሏል ነው ያሉት። በበጋ ስንዴ ልማት ደግሞ 319 ሺህ 547 ሄክታር መሬት በመሸፈን 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።
በእንስሳት ሀብት ዘርፍም 761 ነጥብ 8 ቶን እንዲሁም በወተት ምርት ደግሞ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን በላይ ምርት መገኘቱን ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ከሕገወጥ የማዕድን ምርት ቁጥጥር ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ መሠብሠብ ተችሏል” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next article“ከግብርና ምርት ከ562 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል” አቶ ፈንታው ፈጠነ