
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በጉባኤው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን የ2018 በጀት ዓመት የፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ ነው።
የክልሉን ምርታማነት ማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን መቀነስ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ንግድን በዓይነት እና በመጠን ማሳደግ በቁልፍ ተግባር ተይዘው መከናወናቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የነበሩ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በመሥራት አበረታች ዕድገት ተመዝግቧል ነው ያሉት። የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል፣ የመሪዎች እና የሠራተኛው ትጋት እና አሻጋሪ የዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ተግባራዊ በመደረጉ የመጣ ለውጥ ነውም ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም አብራርተዋል። የዋጋ ግሽበትን ወደ 8 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉንም ተናግረዋል።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳለጥ፣ የመንግሥት ድጎማ እና ከቀረጥ ነጻ ማሻሻያዎችን በመተግበር፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሻሻል እና የግብርና ምርታማነቱን በማሳደግ የዋጋ ግሽበቱ እንዲቀንስ መደረጉን አንስተዋል።
ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም እና በልዩ ልዩ የገጠር እና የከተማ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ አማራጮች በክልሉ ለ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቋሚ እና በጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሯልም ብለዋል።
ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠን እና በጥራት ለማስፋት በተሠራው ሥራ ከ562 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ተችሏል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በማዕድን እና በቱሪዝም ዘርፎች ከ796 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ርእሰ መሥተዳድሩ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
