
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው መክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የምክር ቤቱ አባላት በምርጫ ዘመኑ በምክርቤቱ የነበራቸው ተሳትፎ የላቀ እንደነበር አንስተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ለሕዝብ ሲሉ ሀሳባቸውን ሳይሰስቱ ሲሰጡ እንደነበርም ጠቁመዋል። ያደርጉት የነበረው የክትትል እና ድጋፍ ሥራም መሠረታዊ እንደነበር አንስተዋል። የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በማንሳት በምክር ቤቱ ገንቢ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሎም ከችግር አዙሪት ለመውጣት የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ ሢሠራ መቆየቱን አንስተዋል።
በዕቅዱ እና በአፈጻጸሙ ላይ የምክር ቤቱ አባላት እና ቋሚ ኮሚቴዎች ሀሳብ በመሥጠት ሰፊ ክትትል አድርገዋልም ነው ያሉት።
ግጭት እና ጦርነት የክልሉን የመልማት አቅም ወደ ኋላ እየጎተተው ነው ያሉት ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ግጭትን በውይይት እና በንግግር መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በቀጣይ በ7ኛው ዙር የምክር ቤት ዘመን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን መተግበር የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ለመፍታት እንደሚያግዝም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
