በነሐሴ አጋማሽ የሚከበሩ በዓላት ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ዝግጅት ተደርጓል።

8
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ እና የአማራ ክልል ባህል፣ ኪነጥበብና ዝክረ ታሪክ ጽሕፈት ቤት በ2018 በጀት ዓመት በከተማ ክላስተር የተከናወኑ ሥራዎችን እና በነሐሴ አጋማሽ የሚከበሩ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላትን አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ እምቢያለ እንደገለጹት፤ በ2018 በጀት ዓመት በከተሞች በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የባሕል ተቋማት፣ ቤተ መጻሕፍት፣ አምፊ ቲያትሮች እና ታሪክ ለሠሩ ታዋቂ ሰዎች የመታሰቢያ ሐውልቶች ተገንብተዋል ብለዋል።
በተመሳሳይም ከተሞችን ለነዋሪዎችና ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ ሥራ በስፋት መከናወኑን ጠቅሰው፣ በ2018 በጀት ዓመት ክልሉን ከጎበኙ 18 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች 15 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተገኘ ገልጸዋል።
ከሐምሌ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በክረምት የሚከናወኑ ተግባራት በዕቅድ መሠረት እየተፈጸሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በነሐሴ አጋማሽ የሚከበሩ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል ፣ ቡሄ እና ደብረታቦር በዓላት ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ዝግጅቶች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ኪነጥበብና ዝክረ ታሪክ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በላይ ስማቸው በበኩላቸው፤ ተቋሙን ለተመራማሪዎችና ለጎብኝዎች የበለጠ ምቹና ሳቢ በሆነ መልኩ ማደራጀት መቻሉን ገልጸዋል።
የጽሕፈት ቤቱ ኤግዚቢሽን የጥንታዊ፣ የመካከለኛና የዘመናዊ ታሪክ ክፍሎች ተብሎ በአዲስ መልክ ተደራጅቷልም ብለዋል።
ተቋሙ የክልሉን ባሕልና እሴቶች ለማስጠበቅና ለማስተዋወቅ በትኩረት እየሠራ ሲሆን፣ በቲያትርና በሙዚቃ ዘርፍ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በተደረጉ ተሳትፎዎች ክልሉን በስፋት ማስተዋወቅ መቻሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በባሕልና እሴት ግንባታ የተጀመሩ ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ።
Next articleዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።