
የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተና ጄነራል መሐመድ ተሰማ ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ከፍተኛ መሪዎች ጋር ዞኑ ባከናወናቸው የሰላም ተግባራት ዙሪያ መክረዋል። በቀጣይ የጋራ ዕቅዶች ላይም አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
በ2015 ዓ.ም ገጥሞ ከነበረው የሰላም እጦት ችግር በመውጣት ዛሬ ላይ በቀጣይ ዕቅዶች ላይ ለመነጋገር የተቻለው የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች እና የጸጥታ አካላት ሕዝብን ለማገልገል ቁርጠኛ ኾነው ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት መኾኑን አዛዡ ተናግረዋል።
“አሁን ግዳጅ እየፈፀምን ያለነው የኢትዮጵያን መፍረስ ከሚሹ ኃይሎች እና ባንዳዎች ላይ ነው” ብለዋል። እየተደመሰሰ ያለው ፅንፈኛ ቡድን ታሪካዊ የሀገር ጠላቶችን ለማንገስ የሚውተረተር ስለመኾኑም ጠቁመዋል። የጥፋት መልዕክተኛውን ሴራ ማክሸፍ ማለት የኢትዮጵያን ሰላም እና ልማት ማረጋገጥ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
እነዚህ የፅንፈኛው አዝማቾች በጀግኖች አባቶቻችንም ኾነ በዚህ ትውልድ ደጋግመው የተሸነፉ፣ በራሳቸውም ኾነ በባንዳዎች ለዘመናት የዕጅ አዙር ጥቃት ቢሰነዝሩም እየተደቆሱ ህልማቸው የመከነባቸው ብረት አምላኪዎች መኾናቸውን አስገንዝበዋል።
ታሪካዊ ጠላቶች ዛሬም ይህንን ፅንፈኛ ኃይል በማደራጀት፣ በማስታጠቅ እና በማዝመት ሥልጣንን በዕጃችን እናስገባለን የሚለው ዲስኩራቸው እንደ ጉም በኖ መቅረቱንም ሌተና ጀነራል መሐመድ ተሰማ አንስተዋል።
ሀገራዊ ምርጫውን ለማደናቀፍ አቅማቸውን አሟጠው ቢፍጨረጨሩም እነሱም ተመተው ሕዝቡም የሚበጀውን መርጦ ሁለት ሽንፈት ተከናንበዋል ነው ያሉት።
በአሁኑ ሰዓት ባዕዳን ጠላቶች ቅጥረኞችን እየገዙ ቢያሰማሩም የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሕዝቡ ባደረጉት ተጋድሎ ጠላቶች እየተመቱ፣ አስታጣቂዎቹም ተስፋ እየቆረጡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በጽንፈኛው ላይ ባሳረፈው ጠንካራ ምት አሁን ላይ በዞኑ በሰፈነው ተነጻፃሪ ሰላም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የልማት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ሕዝቡም በመንቀሳቀስ የመንግሥት እና የግል ድርጅቶችን አገልግሎቶች ያለችግር ማግኘት ችሏል፡፡
ጠላት ተመትቶ በአንድ ቦታ መዋል ማደር የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ ተስፋ እየቆረጠ ነው፤ ይህም የኾነበት ምክንያት ሠራዊቱ እና ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባመጡት ድል ነው ብለዋል አዛዡ።
ፈጣን ተንቀሳቃሽ የፀረ ሽምቅ ስምሪት በሚሠራበት በዚህ ወቅት፣ የድሉን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የፀጥታ ኃይሎች፣ ወረዳ-ከወረዳ በኦፕሬሽን ግዳጁ እና ጽንፈኛውን ከሕዝብ በመነጠል ተግባራቱ ተቀናጅተው እኩል ስምሪታቸውን በመፈጸም ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ሌተና ጀነራል መሐመድ ተሰማ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሠራዊቱ በየጥሻው የተሰገሰገውን ጽንፈኛ ቡድን የገባበት በመግባት የመመንጠር ግዳጁን በብቃት እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ከክልሉ ሕዝብ እና የፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ሕግ የማስከበር ተልዕ አስተማማኝ ሰላም እስኪመጣ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው እንዳሉት ባለፉት ሶስት ዓመታት ቀጣናው ከሰላም እጦት ረደጋ ወጥቶ ዛሬ በዚህ ደረጃ መወያየት የተቻለው መከላከያ ሠራዊት በከፈለው መስዋዕትነት ነው። በመሆኑ ክብር እና አድናቆት እንሰጣለን ብለዋል።
ዘገባው የምስራቅ ዕዝ ነው።
#ባሕርዳር ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
