
ሞትን የናቁላት፤ በጠላቶችዎ ፊት ስለ ፍቅሯ የመሰከሩላት፤ በሞት አፋፍ ላይ ኾነው በጽናት የቆሙላት፤ በጥይት አረር የተጠበሱላት፤ እስከ ሞት ድረስ የወደዷት፤ ቃል ኪዳንም ያስቀመጡላት፤ ትውልድ ሁሉ በጠላት እንዳይገዛ አደራ ያሉባት አባት ኾይ የሀገር ፍቅር እንደምን ያለች ናት ?
መከራን የታገሱላት፣ በሀሰተኞች ፊት ቆመው መራራዋን ፍርድ የተቀበሉላት፤ አስከፊዋን ጽዋ የተጎነጩላት፣ ሀገሬን አትንኩ እያሉ ሊገድሉዎት ከቆሙ ጠላቶቿ ፊት በድፍረት የቆሙላት ሀገርዎትን እንዴት አድርገው ቢወድዷት ነው ?
ሞትን ሲያዩት፤ የገዳዮችን መሻኮል ሲመለከቱት፤ የጠላቶችዎን ጭካኔ እና በሀገሬው ሰው የሚደርሰውን በደልና ግፍ ሲታዘቡት ምን ተሰምቶዎት ይኾን ? በጠላቶችዎ ጭካኔ እስኪሞቱ ድረስ ስንት ማዕልትን እና ስንት ሌሊቶችን ለሀገርዎ እና ለሃይማኖትዎ አለቀሱ ? በግፍ ያልቁ ስለነበሩት የመንፈስ ቅዱስ ልጆችዎስ ምን ያክል አነቡ ?
ብጹዕነትዎ ኾይ ሃይማኖትዎን የወደዱበት መውደድ እንደ ምን ያለ መውደድ ነው? ሀገርዎን ያፈቀሩበት ፍቅርስ እንደምን ያለ ፍቅር ነው? ታማኙ እረኛ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ከበጎችዎ ቀድመው ወደቁ።
ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ስለ ኢትዮጵያ ሀገራቸው፣ ስለተወደደች ሃይማኖታቸው በፋሽስት ጣሊያን ሰማዕትነትን የተቀበሉ ሰማዕት ናቸው።
ዲያቆን መርሻ አለኸኝ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን በተሰኘው መጽሐፋቸው ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕረገ ጵጵስና ካገኙ አምስት ኢትዮጵያውያን አባቶች መካከል አንደኛው ናቸው ብለው ጽፈዋል። ግንቦት 18 /1921 ዓ.ም በእሰክንድርያ መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርሰቲያን መዓረገ ጵጵሰናን የተቀበሉት ብጽዕነታቸው ቤተክርስቲያን በሰጠቻቸው ሥልጣን መሠረት በአገልግሎታቸው እየተፋጠኑ ባለበት ጊዜ የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ በኢትዮጵያ ላይ በግፍ ተነሳ። በሀገር፣ በሕዝብ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ አያሌ ግፎችን ፈጸመ። ይህን የተመለከቱት ብጹዕነታቸው አዘኑ። ስለ ሀገራቸው እና ስለ ሃይማኖታቸው ክብር ሲሉም መስቀላቸውን ይዘው ታገሉ።
ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ጣሊያን ፋሽስት በኢትዮጵያ ላይ በተነሳ ጊዜ በሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል። ከዘመቻ መልስ በኋላ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገቡ። ከዚያም ኾነው አርበኞችንም በስብከታቸው ያበረታቱ ነበር ብለው ጽፈዋል።
ለፋሽስት ጣሊያን የገቡ ሰዎች ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስን ለጣሊያን እንዲገቡ እና ስብከታቸውን እንዲያቆሙ
ይለምኗቸው ጀመር። እርሳቸው ግን አልቀበልም አሉ።
ሚያዝያ 27/1928ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ በፋሽስት ጣሊያን ወታደሮች ከተወረረች በኋላ ሰላም አልነበራትም። አርበኞቹ አንድ ቀን ከተማዋን ይይዟታል እያሉ ጣሊያኖች ይፈሩ ነበር።
ጣሊያኖች እንደፈሩት አርበኞች ሐምሌ ወር ላይ ድንገት ጥቃት ከፈቱ። አርበኞቹ የሚያስገርም እና ከባድ ውጊያ አደረጉ። ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ሲሄዱም ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ሲደርሱ የጣሊያን ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው። ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ተዋግተው ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ወደኋላ ሲመለሱ ከአርበኞች ጋር የነበሩት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ በጠላቶች እጅ ወደቁ።
ዲያቆን መርሻ አለኸኝ ደግሞ አርበኞች ወደ መጡበት ሲመለሱ ከአርበኞች ጋር የነበሩት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ አዲስ አበባ ከተማን ትተው ለመሄድ አልፈቀዱም። “ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ኾኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ፤ ካልኾነ ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ” ብለው ከአርበኞች ተነጥለው በአዲስ አበባ ቀሩ ብለዋል።
ብጹዕነታቸው ግን ያሰቡትን መፈጸም አልቻሉም። በግራዚያኒ እጅ ወደቁ። ለፍርድም ቀረቡ።
ዲያቆን መርሻ አለኸኝ የኮርየሬ ዴላሴራ ጋዜጣ ወኪል እና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለውን ጋዜጠኛ ዋቢ አድርገው ሲጽፉ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ። የቀረበባቸውም ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምጸዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል የሚል ነበር። ዳኛውም ካህናቱም ኾኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ኾኑ ? በማለት ጠየቃቸው፡፡
ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስም አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው። ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኀላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬ እና ስለ ቤተ ከርስቲያኔ አቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ አውቃለሁ:: ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ አሉ፡፡
በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ አንዲያይ ተጋብዞ ለተሠበሠበው ሕዝብ እንዲህም አሉ አረማዊ የኾነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው እንጂ በጎ ለመሥራት፣ አውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ። ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት አንዳይገዛ አውግዣለሁ። የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰም የተገዘተች ትሁን አሉ ብለው ጽፈዋል።
ጰውሎስ ኞኞ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣን ዋቢ አድርገው ሲጽፉ ከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ። በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ ። ፋሽስቶች የሀገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ። ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሽስት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው። የኢትዮጵያም መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን ብለው ተናገሩ ብለዋል።
ብጹዕነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ሰለእርሳቸው እያዘነ ሳለ መሰቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ተሰማ። በዚህም ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር ተብሎ ተጽፏል።
ጰውሎስ ኞኞ ሲጽፉ አቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርዱ በተፈረደባቸው ጊዜ በጸጥታ አዳመጡ። የሞት ፍርዱ ከተፈረደ በኋላ ኢጣሊያኖች የመግደያውን ቦታ ለማዘጋጀት ወደ ገበያ ሄዱ። የመግደያ ቦታው ተዘጋጅቶ አቡነ ጴጥሮስ ወደ መግደያ ቦታው ተወሰዱ። በመግደያ ቦታው ለገዳዮች ተመቻችተው ቆሙላቸው። በዚህም ጊዜ አንድ አስተርጓሚ ተጠግቶ ዐይንዎ እንዲሸፈን ይፈልጋሉን ? አላቸው። እርሳቸውም የእናንተ ጉዳይ ነው። እንደወደዳችሁ እና እንደፈቃዳችሁ አድርጉ። ለእኔ ማንኛውም ስሜት አይሰጥኝም አሉ ብለዋል።
ከዚያ በኋላ ፊታቸውን ወደ ግድግዳው እንዲያዞሩ ተደረገ። እርሳቸውን ቀድሞ በመግደል ክብር የሚፈልጉት ስምንት ካራሚኜሮች ከአቡነ ጴጥሮስ 20 እርምጃ ርቀው በርከክ አሉ። በአስተኳሹ ትዕዛዝም ተኮሱ። ሀገራቸውን የሚወዱት፣ እስከ ሞት ድረስ ስለ ሀገራቸው እና ስለ ሃይማኖታቸው በጽናት የቆሙት አባት ወደቁ።
ያቺም ቀን ልክ በዛሬዋ ቀን ሐምሌ 22/1928 ዓ.ም ነበር። አባት ኾይ ስለ ከፈሉት መስዋዕትነት ትውልድ ሁሉ ያመሰግንዎታል። ግን አባት ኾይ የሀገር ፍቅር እንደምን ያለች ናት ?
#አሚኮ #የሀገርፍቅር_እስከ_ሞት #አቡነጴጥሮስ
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_22_2018_ዓ_ም
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
