ከአዱሊስ እስከ አሰብ – የኢትዮጵያ የባሕር በር ታሪክና ትግል

10
⚓
ቀይ ባሕር ወደ አፍሪካ፣ ባብ ኤል መንደብ፣ ሜዲቴራኒያን እና ሕንድ ውቅያኖስ የሚያሻግር ከፍተኛ የመርከቦች ትራፊክ የሚያስተናግድ መሥመር ነው። በዚህ የባሕር መንገድ ለመሻገር ለዘመናት የኢትዮጵያም መልካም ፈቃድ ይጠየቅ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ኢትዮጵያ የታላቁ ባሕር አንዷ ባለቤት ስለነበረች።
⚓ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት በታሪክ ማኅደር ያዕቆብ ኀይለ ማርያም (ዶ.ር) “አሰብ የማን ናት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች የታወቀው ከ100 እስከ 150 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ በሚገመተው “የኤርትራ ባሕር ዙሪያ ጉዞ”
(Periplus of the Erythraean Sea) በተሰኘው መጽሐፍ መኾኑን አትተዋል። መጽሐፉ የአክሱም ንግድ በዋናው የባሕር በር በአዱሊስ በኩል ይተላለፍ እንደነበረ አረጋግጧል።
ኮስሞስ (Cosmos) የተባለ ጸሐፊ ደግሞ የክርስቲያን ፎቶግራፊ (Christian Photography) በሚለው መጽሐፍ አዱሊስን መጎብኘቱን እና በጊዜው የነበረው ንጉሠ ነገሥት አጼ ካሌብ እጅግ የዳበረ የባሕር ኀይል እንደነበረው እና ቀይ ባሕርንም ተሻግሮ የመንን እና ደቡብ አረቢያን ይቆጣጠር እንደነበር ገልጿል።
በወቅቱ የአክሱም መዳከም እና የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ሥልጣን ላይ መውጣት ኢትዮጵያን የባሕር በር አላሳጣትም ነበር። አጼ ዘርዓ ያዕቆብም ይበልጥ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነትን በማረጋገጥ ተጠቃሚነታቸውን አጠናክረው እንደነበር በመጽሐፉ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ አዱሊስ፣ ገምበዛ፣ ዘይላ እና ምፅዋ የተባሉ ወደቦችን በማሥተዳደር ገናናነቷን አጉልታ እንደነበርም ታሪክ ይጠቅሳል። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትም በታሪክ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እና ከኤደን ገልፍ ጋር ትዋሰን እንደነበር ገልጸዋል።
በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ማዕከላዊ መንግሥት ከመዳከሙ ቀደም ብሎ በአጼ ፋሲል ህልፈት እና በአጼ በካፋ መንግሥት መካከል ባሉት 65 ዓመታት የኢትዮጵያ የባሕር በር ተዳክሞ ነበር። ኾኖም በአጼ በካፋ፣ በአጼ ኢያሱ ሁለተኛ እና በአጼ ኢዮአስ ዘመነ መንግሥታት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጠረፍ የተጠናከረ ይዞታ እንደነበራት መጽሐፉ አትቷል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ለማስመለስ ከተደረጉ ትግሎች መካከል:-
✍️ የአጼ ቴዎድሮስ ትግል አጼ ቴዎድሮስ እ.ኤ.አ. በ1855 በጥቅምት 20 ጎንደር ላይ ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤ ጥንት የኢትዮጵያ ነገሥታት ባህረ ነጋሽ እያሉ ተጠሪዎቻቸውን ይሾሙበት የነበረውን የቀይ ባህር አካባቢ ወደቦችን የያዙት ቱርኮችን ለማስለቀቅ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ለንግሥቲቱ አስታውቀው ነበር።
ይህንን ለመግለጽ “ቱርኮች የአባቶቼን መሬት ልቀቁ ብላቸው እምቢ ስላሉኝ በእግዚአብሔር ኀይል ይኸው ልታገላቸው ነው፤ ቱርኮች በባህር ላይ ኾነው መልዕክተኛዬን አላሳልፍም ብለው ችግር ፈጥረውብኛል” ሲሊ ለንግሥት ቪክቶሪያ ደብዳቤ ጽፈዋል። ይሁን እንጅ የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት ለማስመለስ የወጠኑት ዓላማ ግቡን ሳይመታ ሞት ቀድሟቸዋል።
✍️የአጼ ዮሐንስ ትግል ከአክሱም ከተማ ሰኔ 10/1872 ዓ.ም ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ አጼ ዮሐንስ በላኩት ደብዳቤ “የምጽዋ በር የአባቶቼ የኢትዮጵያውያኑ ነገሥታት ነው፤ በእርስዎ እርዳታ የምጽዋን በር እንድይዝ ያድርጉልኝ ብዬ እለምናለሁ” ሲሉ ጠይቀዋል። በዘመነ መንግሥታቸውም ለባሕር በር ብዙ ታግለዋል።
✍️ የአጼ ኀይለ ሥላሴ ትግል የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት በአጼ ኀይለ ሥላሴ ብርቱ ትግል ለዓመታትም ቢኾን ተመልሶ ነበር። ከባሕር በሩ ባሻገር ኤርትራም የኢትዮጵያ አንድ አካል ኾና ነበር።
አጼ ኀይለ ሥላሴ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ከመተሳሰሯ 5 ዓመት ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ1947 “አዱሊስ፣ ባህረ ነጋሽ እና ወልወል” ብለው የሰየሟቸውን ሦሥት መርከቦች ገዝተው ቀይ ባሕር ላይ አሰማርተዋቸው ነበር።
በ1952 በኤርትራ ሕዝብ ተወካዮች ፍላጎት እና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተቀላቀለች። ለዘመናት ትግል ሲደረግበት የኖረው የባሕር በር ጥያቄ በአጼ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ዕውን ኾኖ ኢትዮጵያ የሁለት ወደብ ማለትም የምጽዋ እና የአሳብ ባለቤት ኾነች።
በሂደትም ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ የኢትዮጵያ ሙሉ አካል ስትኾን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔ ያገኘ መሰለ። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሳያቋርጥ አንዱ ሥርዓተ መንግሥት ከሌላው እየተዋረሰ ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንዳትገለል አድርገዋል።
ኾኖም ሕወሃት ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿን በመካድ ኢትዮጵያ የባሕር በር አያስፈልጋትም በማለት በሤራ ለዓመታት ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትርቅ አድርጓታል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ በርካታ ገንዘቦችን እንድታወጣ፤ ዕድገቷ እንዳይሳለጥ፤ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳይኾኑ፤ ከባሕር በር የምታገኘው ጥቅም እንዲቀር አድርጓል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በዚህ ዘመን የተነሳ ብቻ አይደለም ለዘመናት በነገሥታቶቿ ሲጠየቅ የነበር ጉዳይ መኾኑን ታሪክ በጉልህ ያስረዳል።
✍️ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአባት ኾይ የሀገር ፍቅር እንደምን ያለች ናት?