
🏭የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የወጭ ንግድ አፈጻጸም ግምገማ እና የላቀ አፈጻጸም ዕውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ እንደተገለጸው ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለው አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
🔍 የውጭ ምንዛሬ ገቢ እና የፋይናንስ አቅርቦት ማደግ
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 607 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ችላለች። ይህ ስኬት ዝም ብሎ የመጣ ሳይኾን፣ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል።
በ2014 ዓ.ም ለዘርፉ የሚቀርበው ፋይናንስ ከ40 ቢሊዮን ብር ያልበለጠ ነበር። በአሁኑ ወቅት ወደ 115 ቢሊዮን ብር ማደጉ ለአምራቾች ትልቅ አቅም ኾኗል።
🛠️ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማነቆዎችን መፍታት
ባለፉት ዓመታት አምራቾች ያጋጥሟቸው የነበሩ የመሠረተ ልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የፖሊሲ ማነቆዎችን ለመፍታት “የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል” ተቋቁሞ የልየታ ሥራ ተካሂዷል። በዚህም መሠረት የ192 ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈቱ ተደርጓል። ይህም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች በየዓመቱ ወደ ምርት እንዲገቡ አመች ሁኔታ ፈጥሯል።
👥 የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ፋይዳ
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መስፋፋት ቀጥተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከ430 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ይህም የዜጎችን ገቢ ከማሳደጉም በላይ በከተሞች ያለውን የሥራ እጥነት ጫና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
🌐 አዲሱ የኤክስፖርት ስትራቴጂ እና የዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነት
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደጠቆሙት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ31 የገበያ ማዕከላት ላይ ምርቶቿን ለማቅረብ የሚያስችል አዲስ የኤክስፖርት ስትራቴጂ አዘጋጅታለች።
ዓላማውም የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ፣ የልዩ ዕድሎችን አጠቃቀም ማሳደግ እና የንግድ ሚዛን ክፍተቱን ማጥበብ ነው ብለዋል።
🚀 የወደፊት ግቦችን በተመለከተ ሲያብራሩ በ2019 በጀት ዓመት ከዘርፉ 1 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።
በ2030 ደግሞ ገበያውን ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር በማሳደግ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ዋና የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ ዕቅድ እንደተያዘ አስገንዝበዋል።
👏 በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ በ2018 በጀት ዓመት ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች የዕውቅና እና ሽልማት መርሐግብር ተካሂዷል። ይህም በቀጣይ ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት ትልቅ ማበረታቻ ይኾናል ተብሏል።
#አማራች_ኢንዱስትሪ #Export #EconomicGrowth
#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_22_2018_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ: አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
