🌿መትከል ብቻ ግብ አይደለም፤ ለፍሬ ማብቃት ያስፈልጋል።🍎🍌

5

 

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በዘላቂነት የሚያለማውን ቦታ ከክልሉ ምክር ቤት ተረክቧል። ርክክቡን ተከትሎም የቢሮው ኀላፊዎች እና ሠራተኞች “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በምክር ቤቱ አዳራሽ ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በዚህ መርሐ ግብር ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለው የደን ሽፋን እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።

በምርምር ማዕከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ለአርሶ አደሮችም ኾነ ለከተማ ነዋሪዎች አርዓያነት ያላቸው፣ በዓመት ከሁለት እስከ ሦሥት ጊዜ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ የሙዝ እና የፓፓያ ዝርያዎች መተከላቸውን ነው የገለጹት። ቢሮው መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በተግባር አርዓያነት ያለው ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።

ቢሮው ከዚህ ቀደም ተተክለው የነበሩ ችግኞችን ተገቢ እንክብካቤ በማድረግ ከ90 በመቶ በላይ የጽድቀት መጠን ላይ እንዲደርሱ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

አዲስ የተተከሉት ችግኞችም እንዲጸድቁ እና ለፍሬ እንዲበቁ በውኃ ፓምፕ ድጋፍ እና በባለሙያዎች አማካኝነት ክትትል ይደረግባቸዋል ብለዋል። መትከል ብቻ ግብ አይደለም ለፍሬ ማብቃት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ተቋማት ለኅብረተሰቡ አርዓያ በመኾን ሠርቶ ማሳየት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ሕንፃ አሥተዳደር እና አጠቃቀም ማዕከል ዋና ሥራ አሥኪያጅ ዓለምነህ ይታየው የአማራ ክልል ምክር ቤት ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት በማድረግ በምክር ቤቱ ግቢ ውስጥ ቋሚ ተክሎችን፣ የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና ቡና በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል። ግቢውን የሥልጠና እና የዘር ብዜት ማዕከል ለማድረግ ታልሞ እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታትም በተሠራው ሥራ በግቢው ውስጥ ከ80 በላይ ሀገር በቀል ዛፎች መኖራቸውን አንስተዋል።

አሁን የተተከሉትን ችግኞች በእንክብካቤ እና በባለሙያዎች ክትትል ዘላቂነት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ይሠራልም ብለዋል።

በምክር ቤቱ ግቢ የሚከናወኑ የችግኝ ተከላ እና የልማት ሥራዎች ለሌሎች አርዓያ በመኾን ልምድ የሚቀስሙበት ማዕከል እንዲኾን ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባለሙያ ፈቃዱ ገድፍ ችግኝ መትከል ሀገራዊ ኀላፊነት ነው ብለዋል። የሚተከሉ ችግኞች የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ድርሻው ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። የተተከሉ ችግኞችን በባለቤትነት እንደሚንከባከቡም ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የቢሮው ባለሙያ ዳሳሽ ጎፋ በምክር ቤቱ ግቢ በመገኘት ለሁለተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማከናወናቸውን ገልጸዋል። የተከላ መርሐ ግብሩ የሀገሪቱን የደን ሀብት ገጽታ የሚያጎላ እና የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው ብለዋል።

ችግኞችን መትከል ጥላ ከመኾን እና ዝናብን ከማስተካከል ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ በመኾኑ የሚተከሉ ችግኞችን ለፍሬ ለማብቃት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

አሚኮ #አማራ_ክልል #green legacy #ኮሙዩኒኬሽን_ቢሮ

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_22_2018_ዓ_ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🕊️ የጠመንጃ አዙሪት በሃሳብ የበላይነት ሲሰበር
Next article📊በበጀት ዓመቱ ከ240 በላይ ለሚኾኑ ተቋማት የኦዲት ሽፋን ተሰጥቷል።