🕊️ የጠመንጃ አዙሪት በሃሳብ የበላይነት ሲሰበር

6

 

ኢትዮጵያ የዘመናት እና የተወሳሰቡ የፖለቲካ፣ የታሪክ እና የማኅበራዊ ልዩነቶቿን በጠመንጃ ሳይኾን በሃሳብ የበላይነት ለመፍታት የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር፤ ሀገሪቱ ካለፈችበት የታሪክ አውድ አንፃር እጅግ የላቀ እና ታሪካዊ ትርጉም አለው። ይህ ጥረት ልዩነትን በኅይል ከመፍታት ይልቅ በሃሳብ የመፍታትን መሠረታዊ እሴት በተግባር የሚያሳይ ነው።

በጠመንጃ የሚገኝ መፍትሄ አሸናፊ እና ተሸናፊን የሚፈጥር፣ የተሻለውን ሃሳብ የሚያፍን እና ጥላቻን ለትውልድ የሚያወርስ ጊዜያዊ ማስታገሻ ነው።

በምክክር የሚመጣ መፍትሄ ግን የጋራ መግባባትን የሚያመጣ፣ ይቅርታ እና አብሮነትን የሚያጎለብት እንዲሁም የተሻለ ሃሳብ የሚደመጥበት ዘላቂ ስምምነት ነው። ይህ ጥረት እውን ኾኖ ግቡን ከመታ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባሕል ከመሠረቱ የመቀየር አቅም አለው።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ ላይ እና በተለያዩ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጠንካራ እና የታፈረች ሀገር የምትገነባው በሀገራዊ መግባባት እንደኾነ አስምረውበታል። በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየውን፤ በግጭት እና በጥላቻ ንግግር ጀምሮ በጦርነት የሚያልቀውን የፖለቲካ ልማድ መስበር የሚቻለው በውይይት፣ በመከባበር እና በሀገራዊ መግባባት ብቻ መኾኑንም አመላክተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በታሪክ፣ በፖለቲካ እና በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ የሀገርን ዘላቂ ሰላም፣ አንድነት እና ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ አለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሂደቱ የአሁኑን እና የነገውን ትውልድ እጣ ፈንታ የሚወስን “አዲስ የታሪክ ምዕራፍ” ነው ብለውታል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ ሊጠቀሙበትና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊያደርጉበት እንደሚገባም ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ጠመንጃን በሃሳብ ለመተካት የሚደረገው ይህ ታላቅ ጥረት ጉልበት ያለው ያሸንፋል የሚለውን አዙሪት በመስበር አክራሪ ትርክቶች፣ የዘመናት ብሶቶች እና የመጻኢ ጊዜ ራዕዮች በጠረጴዛ ዙሪያ በነፃነት የሚንሸራሸሩበትን የሠለጠነ የሃሳብ ገበያ ይፈጥራል።

ታፍነው የቆዩ ብስጭቶች እና ታሪካዊ ቁርሾዎች በጦርነት ሳይኾን በቃላት እና በሃሳብ እንዲተነፍሱ ሲደረግ ጥልቅ ሀገራዊ የሥነ-ልቦና ፈውስ ይፈጠራል።

በኅይል የተገነባ አንድነት በኅይል ሊፈርስ ስለሚችል በውይይት የሚገነባ ጠንካራ ማኅበራዊ ውል መፍጠር ለዘላቂ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ በቀላሉ የማይናወጥ መሠረት ይጥላል። የሂደቱ ስኬት የሚለካው ግን መሬት ላይ በሚያመጣው ዕውነተኛ እርቅ እንደኾነ የሀገራት ተሞክሮ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ምክክሩ አንድነቷ የሰመረላት እና ሰላሟ ለሁሉም በእኩልነት ከጫፍ ጫፍ መንቀሳቀስ ዕድል የሚሰጥ ኢትዮጵያን ለመገንባት ተስፋ ያለው ውይይት እየተካሄደ መኾኑን ተናግረዋል።

ምክክር በድምጽ ብልጫ ውሳኔ የሚተላለፍበት ሳይኾን ልዩነቶችን እያጠበቡ በጋራ እየተግባቡ የሚሄዱበት ሂደት እንደኾነ ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ የእኔ ሃሳብ ከሚለው ዕይታ ይልቅ የእኛ ሃሳብ ወደሚለው የጋራ መግባባት እና መቀራረብ እየተሸጋገሩ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።

#አሚኮ #NationalDialogue #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_22_2018_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበሀረሪ ክልል ጥራቱን የጠበቀ ሕክምና ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next article🌿መትከል ብቻ ግብ አይደለም፤ ለፍሬ ማብቃት ያስፈልጋል።🍎🍌