በሀረሪ ክልል ጥራቱን የጠበቀ ሕክምና ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

4
የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት የጤና ዘርፉን በግብዓት እና በሰው ኀይል በማደራጀት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጿል።
የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር አብዲ አሚን እንደገለጹት ተቋሙ በሽታን በመከላከል እና አክሞ በማዳን ፖሊሲ ላይ ትኩረት አድርጎ ይንቀሳቀሳል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱን የማዘመን ሰፊ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ተጠቁሟል።
በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የማኅበረሰብ ፍላጎት መነሻ በማድረግ መሠረታዊ የመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓቶች አቅርቦት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የአገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማነት ለማሻሻል ግብ ያደረጉ የተለያዩ የዲጂታል ጤና ኢኒሼቲቮችን በበጀት ዓመቱ በጤና ተቋማት ወደ ሥራ በማስገባት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱ ተጠቁሟል።
የባለሙያዎችን የሙያ ሥነ-ምግባር እና የመፈፀም አቅም ማሳደግም ከታቀዱት ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ተቋሙ በክልሉ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን የመከላከል እና የመቆጣጠሩን ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል ሲኾን ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች የዝግጁነት እና የምላሽ ሥርዓትን የማዘመን ሥራዎችም ይሠራሉ ነው ያሉት።
በተለይ የእናቶች፣ የሕጻናት እና የወጣቶች ጤና እንዲሁም ሥርዓተ ምግብን ማሻሻል፣ ማኅበረሰቡ ራሱን ከበሽታ እንዲጠብቅ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የወባ በሽታን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ዶክተር አብዲ አመላክተዋል።
የጤና አገልግሎትን የጥራት ደረጃ በማሳደግ የክልሉን የጤና ቱሪዝም ለማጎልበት እና ምቹ እና ጽዱ የጤና ተቋማት ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
በመጨረሻም በግንባታ ላይ የሚገኙትን የድሬ ጠያራ ጠቅላላ ሆስፒታል እና የሚያይ አጠቃላይ ሁለተኛ ትውልድ ጤና ኬላ ተቋማትን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም የቢሮው ኀላፊ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከታሪክ የተጣላ የትዕቢትና የጥፋት አባት!