ከታሪክ የተጣላ የትዕቢትና የጥፋት አባት!

8
የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ሂደት በርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ሕዝብን ለድህነት እና ለግጭት ዳርገው ከቆዩ አጥፊ አካሄዶች ዋነኛው የሕወሃት የጥፋት ዑደት ነው።
ቡድኑ ሀገር እየመራ ባለበት ጊዜ እና ከበትረ ሥልጣን ወርዶም ሀገር እና ሕዝብን ለተደጋጋሚ ዙር በድሏል። ሀገር ሆደ ሰፊ ኾና “ይቅር” ብትለውም ይህ ቡድን ግን አሁንም ለሌላ የጥፋት ዑደት ማለሙን የተወ አይመስልም።
ቡድኑ ከሕጋዊ የፓለቲካ ፓርቲነት ቀደም ብሎ ቢሰረዝም ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኃላ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አሠራርን ተከትሎ ፓርቲ ኾኖ እንዲመዘገብ የተጠየቃቸውን ሰነዶች ግን ማሟላት ያልቻለ ኾኗል። በዚህም መሰረት ቦርዱ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን ከሰጠ በኋላ ከግንቦት 05/2017 ዓ.ም ጀምሮ ከሕጋዊ ፓርቲነት መዝገብ ሰርዞታል።
ይህንንም የመጨረሻ ውሳኔ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 06/2018 ዓ.ም በጻፈው የመጨረሻ ደብዳቤ ማሳወቁ ይታወሳል።
ይህ ቡድን ከሕጋዊም ኾነ ከሞራላዊ የውክልና ማዕቀፍ ውጭ በመኾኑ ዛሬ ላይ ቆሞ ለነገ ታሪኩ የሚጨነቅ ወይም ለሕዝብ ዕድገት እና ሰላም የሚቆረቆር ድርጅት አይደለም። በምርጫም ይሁን በጦርነት አሸንፎ ሀገር ለመምራት የነበረው ህልም ከንቱ ሲቀር፣ ሕዝብን እርስ በርስ ወደ ማጋጨት፣ ሰላም እና ኑሮንም ወደመበጥበጥ ተራ ሽፍትነት ወርዷል።
ይህ ግጭት ጠማቂ ቡድን ከሕዝብ፣ ከሀገር፣ ከታሪክ እና ከዕውነት የተጣላ ነው። ዛሬ ላይ ቆሞ ሕዝብን የመምራት ወይም ስለ ሰላም የማውራት ሞራላዊም ኾነ ሕጋዊ መብት የለውም።
ቡድኑ ታሪክ አለው ቢባል እንኳን ታሪኩ የደም፣ የዘረፋ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ በብሔር ከፋፍሎ የመግዛት ጥቁር ምዕራፍ ነው።
የዛሬው ዕውነታውም ከፖለቲካዊ ተልዕኮ ውጭ የኾነ ሽፍንፍን የመላላክ፣ ሀገር የመካድ እና ያበላን እጅ የመንከስ ውርደት ነው።
ከሀገሪቱ ሕግ እና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩም ከውጭ ኀይሎች ጋር ሽፍንፍን ግንኙነት እያደረገ ሕዝብን በሰላም እንዳይኖር፣ ልማት እንዳያይ እና ወንድማማችነት እንዳይጠናከር እየጣረ ነው። ግጭትን እንደህልውና ማራዘሚያ የሚጠቀመው ይህ ግትር ቡድን ያደረሰው እና አሁንም የሚመኘው የጥፋት ዑደት በዘላቂ ውርደት እና ጥፋት ውስጥ ተዘፍቆ ለመኖር እንደሚሻ በግልጽ ያሳያል።
🚨ሕዝብ ምን ያድርግ? ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር እና ያለልዩነት ሰላምን ብቻ አጥብቆ መፈለግ አለበት። የዚህ የጥፋት ቡድኑ አካሄድ ኢትዮጵያዊ መልክ እንደሌለው በመረዳት ከሀገር ጎን የቆሙት የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ “ሕወሃት ከሻእቢያ ጋር በመተባበር ትግራይን ወደ ጦር ምድጃ ውስጥ እያስገባት ነው” እንዳሉት ሁሉ በተለይም ሀገር ወዳዱ የትግራይ ሕዝብ የጥፋቱ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ እንደኾነ መረዳት እና በቡድኑ ላይ የጀመረውን “እምቢ ለዳግም ጥፋት” የሚል አካሄድ ማጠናከር አለበት።
መላ ኢትዮጵያውያንም ታሪክን መመርመር፣ የውጭ ጠላቶች የሚመጡብን ውስጣዊ አንድነታችን የላላ በመሰላቸው ጊዜ መኾኑን ከታሪክ መማር ይገባል። እኛ ኢትዮጵያውያን ተለያዩ ሲሉን የበለጠ አንድ ኾነን የምንቆም፣ ተዳክመዋል ሲሉን ይልቁንም ጠንክረን የምንገኝ ሕዝቦች ነን። የነጻነት እና የድል ተምሳሌቶች ኾነን እንጅ ባዕዳ እና ባንዳ ፈትኖን ወድቀን የታየንበት ታሪክም የለንም።
በመኾኑም የዚህን ቡድን ከታሪክ የተጣላ ዕውነተኛ ገጽታ በመገንዘብ፣ ለሰላም፣ ለአብሮነት እና ለነገ የልማት ጉዞ አብሮ በመቆም የትኛውንም የጥፋት አካሄድ መከላከል ይገባል።
✍️ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከአጭበርባሪዎች ይጠንቀቁ!
Next articleበሀረሪ ክልል ጥራቱን የጠበቀ ሕክምና ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።