6
🌾
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በሰባታሚት ቀበሌ “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሬት በጤፍ ዘር የመሸፈን መርሐ ግብር አከናውኗል።
በቀበሌው አሚኮ ያነጋገራቸው ቄስ አዳነ አሰፋ ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የመጡት። ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ይደረግላቸው የነበረው የእህል ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ችግራቸውን እንዳልፈታላቸው አንስተዋል።
አሁን ላይ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት በሚደረገው ሽግግር ተጠቃሚ ከኾኑ ግለሰቦች ውስጥ አንዱ ኾነዋል። በዚህም በኪሎ ተለክቶ ከሚሰጥ እህል ወደ አምራችነት በመቀየራቸው ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። የዘሩትን ዘር በመንከባከብ በቂ ምርት ለማምረት እየሠሩ መኾናቸውንም አስረድተዋል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ተመሥገን ደጋረገ በወረዳው ከተረጅነት ወደ ምርታማት በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በምግብ ራስ ለማስቻል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በሰባታሚት ቀበሌ ተፈናቃዮች ጤፍ እንዲያለሙ ተደርጓል። ከዚያ ባለፈም በቦታው ሁለት ጊዜ እንዲያመርቱ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ በዞኑ የሚገኙ ፀጋዎችን በመጠቀም ተረጅነትን ለማስቀረት እና በምግብ ራስን ለመቻል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
​ የእርዳታ ጥገኝነትን ለማስቆም በወል መሬቶች ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም መሠረት በዞኑ ከ 338 ሄክታር በላይ መሬት ለማረስ ታቅዶ እስካሁን ድረስ 171 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ነው የገለጹት ።
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማስተዋል አሰሙ ዞኑ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት የሚያሸጋግረውን መርሐ ግብር ተፈጻሚ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ድጋፍ ፈላጊዎችን በመለየት እና ቋሚ የሥራ ዕድል በመፍጠር የተረጂዎችን ቁጥር መቀነስ መቻሉን አንስተዋል።
አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም በሚል መርህ ያልታረሱ መሬቶችን ሙሉ በሙሉ በማልማት በቂ ምርት ለማምረት በቅንጅት እየተሠራ ነው። ከኤሊኖ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቀልበስ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን የማልማት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኅላፊ መሠሉ ብርሃኑ የሕዝቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው። ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች በባለቤትነት ከእርሻ ሥራ እስከ ምርት ድረስ በመንከባከብ ተጠቃሚ መኾን ይገባቸዋል ብለዋል።
መርሐ ግብሩ የዜጎችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፤ ከዕርዳታ ፈላጊነት አስተሳሰብ በመላቀቅ የሀገርን የምግብ ሉዓላዊነት እውን ማድረግን ታሳቢ ያደረገ እንደኾነም ተመላክቷል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article🇪🇹የጸረ ሰላም ኅይሎች እንቅስቃሴ በሠራዊቱ እርምጃ እየከሰመ ነው
Next articleበአማራ ክልል የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት እየተሠሩ ያሉት ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው።