🇪🇹የጸረ ሰላም ኅይሎች እንቅስቃሴ በሠራዊቱ እርምጃ እየከሰመ ነው

7

 

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝብን ከጸረ ሰላም ኅይሎች እንግልት በመታደግ ሰላምን እያረጋገጠ መኾኑን፣ በማንኛውም ጊዜ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

የምሥራቅ እዝ እና የሰሜን ምዕራብ እዝ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

የምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽን ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ እንደገለጹት ሠራዊቱ ኅብረተሰቡን ከስቃይ እና እንግልት ለመታደግ ብርድ እና ፀሐይ ሳይል፣ ወጣ ገባ እና አስቸጋሪ በኾኑ ቦታዎች ላይ ሳይቀር ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ይገኛል። እዚህም እዚያም ሾልከው በመግባት ትንኮሳ ይፈጽሙ የነበሩ የጸረ ሰላም ኅይሎች እንቅስቃሴ አሁን ላይ በሠራዊቱ እርምጃ እየከሰሙ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።

ሠራዊቱ ይህንን ሀገር የማረጋጋት ግዳጅ ሲፈጽም በዘፈቀደ ሳይኾን ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጦርነት ሕጎችን እና የግዳጅ አፈጻጸም ሥነ ሥርዓቶችን አክብሮ መኾኑን ገልጸዋል። ሠራዊቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሕግን ተከትሎ እንዴት ግዳጁን እንደሚፈጽም ትክክለኛውን መረጃ እና ምስክርነት መስጠት የሚችለው ራሱ ሕዝቡ መኾኑንም አመላክተዋል።

ከሀገር ውስጥ ጸጥታ ማስከበር ተግባሩ ባለፈ ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በማንኛውም አቅጣጫ ለሚሰነዘር ትንኮሳ ሙሉ ዝግጅት እንዳለው አረጋግጠዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ ብቃቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ፣ የሰው ኅይሉን እያጎለበተ፣ የግዳጅ አፈጻጸሙን ከሚያቀላጥፉ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር እያስተሳሰረ የሚገኝ ጠንካራ ተቋም መኾኑንም ጠቁመዋል።

በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባው ሠራዊት መቼም ቢኾን በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንደማይደራደር፣ በጠላት ፕሮፓጋንዳ ተሸንፎ ወደ ኋላ እንደማይል እና በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ በተጠንቀቅ ቆሞ ግዳጁን እየፈጸመ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

#የኢትዮጵያ_መከላከያሠራዊት

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_20_2018_ዓ_ም

✍️ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ25 ዓመት ሀገር አቀፍ የኀይል ስርጭት ማሻሻያ እና ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ጥናት ይፋ አደረገ።
Next article