የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ25 ዓመት ሀገር አቀፍ የኀይል ስርጭት ማሻሻያ እና ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ጥናት ይፋ አደረገ።

15
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያደገ የመጣውን የኀይል ፍላጎት ለመሸከም፣ የኔትወርክ ችግሮችን በተቀናጀ ሁኔታ ለመፍታት እና የሀገሪቱን የኀይል ስርጭት ስርዓት ወደ ዲጂታል አሠራር ለማሻገር የሚያስችል የ25 ዓመት ሀገር አቀፍ የኀይል ስርጭት ማሻሻያ እና ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ጥናት አስጠንቷል።
ጥናቱን ያጠናው የኢራኑ ሞኔንኮ ኩባንያ ሲኾን ወርልድ ባንክ ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል:: ማስተር ፕላኑ እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2049 የዕቅድ ጊዜን ይሸፍናል።
ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ሞኔንኮ በጋራ በሠሩት ሥራ የአካባቢ ዕውቀትን ከዓለም አቀፍ አማካሪነት ልምድ ጋር በማቀናጀት የኢትዮጵያን የኀይል ማከፋፊያ መሠረተ ልማት ዘመናዊ ማድረግ እና በረጅም ጊዜ ልማት ለመደገፍ እየሠሩ መኾኑን የኢራን ሞኔንኮ የኀይል ማከፋፈያ ክፍል ኀላፊ ሳራ ናምዳር ተናግረዋል።
ጥናቱ የመጭውን 25 ዓመታት የኀይል ፍላጎት ለማወቅ፣ የኤሌክትሪክ መስመር ትራንስፎርመር የኀይል ጭነት ትንበያ፣ የአካባቢ እና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ምዘና እንዲኹም የመሠረተ ልማቶችን በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር የሚያግዝ እንደኾነ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ናቸው።
ጥናቱ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን፣ ፈጣን የከተማ ዕድገት፣ የነፍስ ወከፍ የኢነርጂ ፍላጎትን እና ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚጠይቀውን የኤሌክትሪክ ኀይል ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲደረግ በኢትዮጵያ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነት ይኖራል። ከነበረው 4 ሺህ 289 ሜጋ ዋጋ የኀይል ፍላጎት በ2049 በመላ ሀገሪቱ ወደ 39 ሺህ 327 ሜጋ ዋት የኀይል ፍላጎት ከፍ እንደሚል በጥናቱ ተመላክቷል።
ፕሮጄክቱን ለማሳካት 30 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግም በጥናቱ ተገልጿል።
ዘጋቢ: ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article📌 የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ የደኅንነት ማዕከል ነው።
Next article🇪🇹የጸረ ሰላም ኅይሎች እንቅስቃሴ በሠራዊቱ እርምጃ እየከሰመ ነው