📌 የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ የደኅንነት ማዕከል ነው።

8

 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ፋናወጊ፣ የፓን አፍሪካኒዝም ማዕከል እና የነጻነት ምሳሌ እንደመኾኗ መጠን የውስጥ ሰላሟ ከድንበሯ ተሻግሮ ለጠቅላላው የአፍሪካ ቀንድ እና ለአህጉሩ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።

ሀገሪቱ የምትገኝበት ስትራቴጂካዊ ቦታ፣ የሕዝቧ ብዛት፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ውስጥ ያላት የመሪነት ድርሻ የኢትዮጵያን ሰላም የጠቅላላው ቀጣና ሰላም መሠረት ያደርገዋል።

🕊️ ሀገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላም ብቸኛው መንገድ ነው። በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መሳካት ለሀገሪቱ የውስጥ አንድነት ብቻ ሳይኾን ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ምዕራፍም ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እና ሌሎች የኮሚሽኑ መሪዎች በተደጋጋሚ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት የቆዩ መሠረታዊ ሀገራዊ ልዩነቶችን እና ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ እና በንግግር መፍታት የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ ነው።

ምክክሩ በሕግ የበላይነት እና በጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ጠንካራ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማደራጀት የመሳሪያ ግጭቶችን እና የውስጥ አለመረጋጋቶችን ለማስቀረት ያለመም ነው።

🌍 የአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምክክር በቅርበት የሚከታተሉ እና ድጋፋቸውን የሚያሳዩ አካላት ናቸው። የኅብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ምክክሩ በተጀመረበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ሰላም ለአፍሪካ ማዕከላዊ ደኅንነት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ ሂደት “አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ” የሚለውን ታላቅ የመተጋገዝ መርሕ በተግባር የሚያሳይ ነው።

🎯 የምክክሩ ስኬት ለቀጣናው ያለው ትርጉም ዘርፈ ብዙ ነው። ከዚህ መካከል ደኅንነትን ማስጠበቅ ይጠቀሳል። በምሥራቅ አፍሪካ የሚታዩትን እንደ አልሸባብ ያሉ የሽብር ቡድኖች ስጋት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመግታት ጠንካራዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ ናት።

የውስጥ ሰላም መስፈን የስደት እና የተፈናቃዮችን ቁጥር በመቀነስ በጎረቤት ሀገራት ላይ የሚፈጠርን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናም ይቀርፋል። የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠርም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ የኢኮኖሚ እና የንግድ ማዕከል በመኾኗ ሰላሟ መረጋገጡም ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስኬት ትልቅ አቅም ይኾናል። በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ ላሉ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ፖለቲካዊ አርዓያም ይኾናል።

በአጠቃላይ የምክክሩ ስኬታማነት የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ቁስል ከመፈወሱ ባሻገር፣ ለአፍሪካ ቀንድ እና ለጠቅላላው አህጉር ዘላቂ ሰላም እና ልማት መሠረት ይጥላል። ስለኾነም የምክክሩ መሳካት የኢትዮጵያውያን ፍላጎት ብቻ ሳይኾን የአፍሪካውያን እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የጋራ ምኞት ነው።

#EthiopiaNationalDialogue

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_20_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ ሰላም እና ደኅንነትን የማረጋገጥ የጎላ ታሪክ አላት።