
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው የ2026 የአፍሪካ ሎጂስቲክስ እና ኮሙዩኒኬሽን ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ ሙሃመድ ኢትዮጵያ ሰላም እና ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ የጎላ ታሪክ ያላት ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ አህጉራዊ መድረክ እንድታስተናግድ መመረ በቀጣናዊ ሰላም ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እና ዓለም አቀፍ መድረኮችን የማስተናገድ ከፍተኛ አቅሟን የሚያሳይ መኾኑን ተናግረዋል።
ሲምፖዚየሙ የትብብር ግንኙነትን የሚያጠናክር ከመኾኑም በላይ ከአጋር ሀገራት የሚገኙ መልካም ተሞክሮዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የሎጂስቲክስ እና የኮሙዩኒኬሽን አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአጋር ሀገራት በማካፈል በአህጉራዊ ሰላም እና ደኅንነት ዘርፍ የምታደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
የአሜሪካ አፍሪካ እዝ ኮማንደር ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን መድረኩ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ፣ የተሻሉ አሠራሮችን ለመቅሰም እና ለወደፊት የሚያጋጥሙ የሎጂስቲክስ እና ኮሙኒኬሽን ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር መድረኩን ማዘጋጀቷ መልካም እንደኾነ ገልጸዋል። ለሲምፖዚየሙ መሳካት የተደረገውን ዝግጅት አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጠንካራ የትስስር መረቦችን መገንባት የሀገራትን አቅም ከፍ ለማድረግ እና ለበለጠ ደኅንነት መሠረት መኾኑን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ተሳታፊ ሀገራት አቅሞቻቸውን በመገምገም፣ ክፍተቶችን እና ተግዳሮቶችን በጋራ በመለየት ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በሲምፖዚየሙ 40 ሀገራት እና 26 ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አጋሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
#አሚኮ #Ethiopia #LogisticsAndCommunication
#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_20_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ: ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
